ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ልማትና ሰላም መረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

210

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፦ ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ልማትና ሰላም መረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።

1 ሺህ 498ኛው የነብዩ መሀመድ የመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጊድ "የይቅርታው ነብይ’’ በሚል መሪ ቃል የእስልምና ሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሌሎች ሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።


 

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ፈትሁዲን ሃጂ ዘይኑ በዚህ ወቅት፤ የመውሊድ በዓልን ስናከብር በሰላም፣ በፍቅርና የህዝብ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ መሆን አለበት ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ልማትና ሰላም መረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት በቀጣይም ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የታላቁ አንዋር መስጂድ ኢማም ሼህ ጧሃ ሀሩን በበኩላቸው፤ መውሊድ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የአንድነት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ መውሊድን ሲያከብር በነቢዩ መሃመድ አስተምህሮት መሰረት በትህትና፣ በይቅር ባይነትና በመተጋገዝ፣ አቅመ ደካሞችን በመርዳት እንዲሁም ከሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖች ጋር አብሮነትን በማጠናከር መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፤ የመውሊድ በዓል ሲከበር የነብዩ መሀመድ ይቅር ባይነት፣ ትህትናና ሌሎች የበጎነት እሴቶችን በሚያንጸባርቅ መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

እንደ ሀገር የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመነጋገር የመፍታት ባህልን በማዳበር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና ለማህበረሰባዊ እድገት መሳካት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ነው የቢሮ ኃላፊዋ የተናገሩት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም