የመውሊድን በዓል ስናከብር  አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን  ይገባል  - የጋምቤላ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

ጋምቤላ፤ መስከረም 16/ 2016(ኢዜአ)፡- የመውሊድ በዓልን ስናከብር  የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶቻቸንን  በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል ሲሉ  የጋምቤላ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት  ምክትል ፕሬዚዳንት ገለጹ።

1 ሺህ 498ኛው የመውሊድ በዓል በጋምቤላ  ክልል በተለያዩ መስጊዶች በድምቀት ተከብሯል።

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሲራጅ አማን በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ ያለው ለሌለው በማካፈልና በመተባበር ሊሆን ይገባል።

በተለይም ዕለቱ የመውሊድ በዓል ብቻ ሳይሆን የክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የመስቀል ደመራ ጭምር የሚከበርበት ድርብ በዓል በመሆኑ ትልቅ ቀን ነው ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሠረት በመተዛዘን፣ በመከባበር፣የተቸገሩትን በማብላትና በማጠጣት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

የመውሊድ በዓል በተለያዩ ምክንያቶች የተራራቁት የሚገናኙበትና የተጣሉ የሚታረቁበት   የፍቅርና የደስታ  ነው ብለዋል።

ህዝቡ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር ያለውን አብሮነትና አንድነት ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጋምቤላ ከተማ አንዋር መስጂድ በዓሉን ሲያከብሩ ኢዜአ ካነጋገራቸው መካከል ሀጂ ሐሰን ሙሀመድ በሰጡት አስተያየት፤  የመውሊድ በዓል የእዝነት፣ የመተሳሰብና የፍቅር ቀን መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን የተቸገሩትን በመደገፍና በአብሮነት እያከበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሁሉም ያለውን በማዋጣት የተቸገሩትን በማብላትና በመደጋገፍ በዓሉን በአንድነት እያከበሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አብዱልባይሰጥ ኢሳ ናቸው።

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም