የመውሊድ በዓልን በመረዳዳት፣ በሰላምና በፍቅር እያከበርን ነው - በሐረር ከተማ የሚገኙ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የመውሊድ በዓልን በመረዳዳት፣ በሰላምና በፍቅር እያከበርን ነው - በሐረር ከተማ የሚገኙ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች

ሐረር ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፦ የመውሊድ በዓልን በመረዳዳት፣ በሰላምና በፍቅር እያከበሩ መሆኑን በሐረር ከተማ የሚገኙ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ተናገሩ።
1ሺህ 498ኛው የመውሊድ በዓል በሐረሪ ክልል ዛሬ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክንውኖች ደምቆ ተከብሯል።
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኢብራሂም መሃዲ እንደተናገሩት ነቢዩ ሙሐመድ የተወለዱበትን የደስታ ቀን የሆነውን የመውሊድ በዓልን በድምቀት እያከበሩ ነው።
የእስልምና አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት በዓሉን ከሁሉም ጋር በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በአብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እያከበሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
''እስልምና የሰላምና ተቻችሎ የመኖር ኃይማኖት ነው'' ያለችው ወጣት ረውዳ መሀመድ በዓሉን በአብሮነት እያከበሩ መሆኑን ተናግራለች።
"በዓሉን የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳትና በመንከባከብ አከብረዋለሁ'' ስትል ገልጻለች።
በዓሉን እያከበረ ያገኘነው ወጣት መሀመድ ኢብራሂም ጥላቻን እና ክፋትን በማራቅ እና ፈጣሪያቸውን በማወደስ በዓሉን እያከበረ እንደሚገኝ ተናግሯል።
መውሊድን አስተምህሮቱ በሚያዘው መሰረት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ባህልን በሚያጠናክሩ ተግባራት እንደሚያከብር ገልጿል።
''በዓሉን በየዓመቱ ሃብታም ደሃ ሳንል ያለ ልዩኑት በአብሮነት እያከበርነው ነው'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ቤኒት መሀመድ ናቸው።
ነቢዩ ሙሐመድ በሚያዙት መሰረትም ረዳት የሌላቸውን እና አቅመ ደካማ ወጎኖችን በመርዳትና በመደገፍ በዓሉን እንደሚያከብሩት ገልጸዋል።
በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በከተማው ሸዋበር በዓሉ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክንውኖች ተከብሯል።