የመስቀል በዓል የአብሮነትና የተስፋ ተምሳሌት ነው”- የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፦ “የመስቀል በዓል የአብሮነት እና የተስፋ ተምሳሌት ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።

የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

“የመስቀል በዓል በምድር ልምላሜ ደምቆና በአደይ አበባ ፈክቶ፣ በልጆች ባህላዊ ጨዋታ፣ በታላላቆች ምርቃትና ምስጋና ታጅቦ በአደባባይ ላይ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።

በዓሉ በክረምቱ ደመና ተጋርዳ የቆየችው ፀሐይ ከምድር ልምላሜ ጋር ተዋሕዳ ደማቅ የብርሐን ጸዳል የምትጎናጸፍበት፣ ምድር የተሰጣትን ዘር አብቅላ እሸት መለገስ የምትጀምርበት፣ ሰዎች ከድባቴ ወጥተው አያሌ ተስፋዎች የሚሰነቁበት ወቅት በመሆኑ የተለየ ድምቀት አለው።

ስለሆነም የመስቀል በዓል የአብሮነት፣ የትጋት፣ የጽናት፣ የትዕግሥትና የተስፋ ተምሳሌት ነው። እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችም በአብሮነት ጉዟችን የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በተስፋ፣ በትዕግሥት፣ በጽናትና በትጋት በማለፍ የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል ለማሳመር በቁርጠኝነት መነሣትና መሥራት ይጠበቅብናል።

የመስቀል ደመራ ሲለኮስ ከፍተኛ ብርሃን፣ ታላቅ ድምቀት እና ውበት ይሰጣል፤ ተስፋንም ይሰንቃል። እኛ ኢትዮጵያዊያንም እንደ ደመራው ነን። እንደ ችቦው ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋ፣ ስነልቦና እና ወጥ መልክአምድር ያላቸው ዜጎች ተሰባስበው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች እንደ ችቦዎች ኅብር ፈጥረውና ተደምረው ታላቋን ኢትዮጵያን እውን እንድትሆን አድርገዋል። ችቦዎቹ ኅብር ፈጥረው እንዲቆሙ የሚያችሉት አምዶች ደግሞ አገር በጽኑ መሠረት ላይ እንድትቆም ከሚያደርጉ የጋራ እሴቶቻችን ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው።

በመሆኑም ተደምረንና ተጋምደን በአብሮነት ለሰላምና ለልማት መረጋገጥ ከተነሳን እንደ ደመራው ብርሃን ከፍ ብለንና ደምቀን እንታያለን። በዙሪያችን የከበበን የልዩነት ጨለማ ይገፈፋል።

ስለሆነም በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች በልዩ ልዩ ክንውኖች ታጅቦ የሚከበረው የመስቀል በዓል ከእርስ በርስ ግጭት፣ ከመጠላለፍ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ከመነሳሳት፣ ከመጨካከን እና ከሌሎችም አፍራሽ ተግባራት ራሳችን አርቀን በወንድማማችነት፣ በአብሮነት፣ በበጎነት፣ በመከባበር፣ በመደጋገፍና በመመካከር ለአገረ መንግሥት ግንባታና ለጋራ ዕድገት እንድንዘጋጅ በዚሁ አጋጣሚ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም