በዓሉን ስናከብር  ለሠላምና ለአብሮነት መጠበቅ  የበኩላችንን ለመወጣት  በመነሳሳት ሊሆን ይገባል- የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ 

ወልዲያ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፡- የመውሊድ በዓልን ስናከብር ለአካባቢያችን ብሎም ለሀገራችን ሠላምና አብሮነት መጠበቅ  የበኩላችንን ለመወጣት በመነሳሳት ሊሆን ይገባል ሲሉ የሰሜን ወሎ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሃጅ አሊጋዝ አስረስ ገለጹ። 

1 ሺህ 498ኛው የመውሊድ በዓል  በዞኑ ሐብሩ ወረዳ ዳና መስጂድ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በደማቅ ስነ-ስርዓት ተከብሯል።

የዞኑ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤  በሀይማኖቱ አስተምሮ መሰረት ህዝቡ ሠላሙንና አብሮነቱን እንዲያጠናክር  በማስተማርና በመምከር የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር  ለአካባቢያችን ብሎም ለሀገራችን  ሠላምና አንድነት   መጠበቅ የበኩላችንን ለመወጣት በመነሳሳት  ሊሆን ይገባል ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ ያለው ለሌለው በመረዳዳት፣ በመተጋገዝና በመተሳሰብ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል። 

በዓሉን ለማክበር ከደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሪ ወረዳ የመጡት ሸህ አህመድ ዳውድ በበኩላቸው፤ የመወሊድ በዓልን ስናከብር ነብያችን ሰለ ሠላም አስፈላጊነት ለተከታዮቻቸው ያስተማሩትን በማሰብ ነው ብለዋል።

ሠላም ከሌለ ወጥቶ መግባትና ሠርቶ መብላት ስለማይኖር ሠላምን ለማስከበር ሙስሊም አባቶች የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ አስታውቀዋል።

ከወልዲያ ከተማ 06 ቀበሌ የበዓሉ ታዳሚ  ወይዘሮ ፋጢሚ ሲራጅ በሰጡት አስተያየት፤ በዓሉን በደስታ እያሳለፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዓሉ እያከብርን ያለው እርስ በእርስ በመረዳዳት ነው ብለዋል።

 የመውለድ በዓል በሰሜን ወሎ ዞን ሐብሩ ወረዳ ዳና መስጂድ በደማቅ  ሥነ-ሥርዓት በተከበረበት ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የእምነቱ ተከታዮች ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም