አንጮቴ፣ ጩምቦና መስቀል በምዕራብ ኦሮሚያ

አንጮቴ፣ ጩምቦና መስቀል በምዕራብ ኦሮሚያ

በአቤኔዘር ፈለቀ

(ከነቀምቴ ኢዜአ)

ወርሃ መስከረም  ምድር በአደይ አበባ ፈክታ የምትደምቅበት፣ የአዕዋፍት ዝማሬ በተለየ ቅላጼ የሚደመጥበት፣ አርሶ አደሩ የልፋቱን ዋጋ ከደጅ-ከማሳው የበቆሎ፣የአተር፣ የባቄላ ወዘተ እሸት የሚቋደስበት፤ በክረምቱ ዝናብ ከአፍ እስከ ገደባቸው ሞልተው 'ከእኔ ወዲያ ላሳር' በሚል የሰዎችን እንቅስቃሴ ገድበው የቆዩ ድፍርስ ወንዞች ጎለውና ጠርተው ሰው ከወዳጅ ዘመዱ የሚገናኝበት "መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ" ተብሎ የተቀነቀነለት የኢትዮጵያዋን የአዲስ ዓመት ብስራት የሚበሰርበት ነው። በመስከረም ወር ከሚከበሩ  ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት አንዱ የደመራና የመስቀል በዓል ነው። መስቀል በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር አውዳመት ነው። 

በተለይ የመስቀል ዋዜማ የሆነው የደመራ በዓል የእምነቱ ተከታዮች ችቦ ለኩሰው በደመቀ ሥነሥርዓት የሚያከብሩት ሲሆን፤ ከትውልድ ቀያቸው ርቀው የሚገኙና ኑሯቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ  ያደረጉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሰባባሰቡበት፣ የተለያዩ አገሮች ቱሪስቶች የሚታደሙበት ነው።  በዓሉ የእምነቱ ተከታዮች በየአካባቢያቸው የእምነቱ ተከታይ ካልሆኑ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ተሰባስበው በአንድነትና በአብሮነት  ለአውዳመቱ የተዘጋጀውን እና ቤት ያፈራውን ባህላዊ ምግቦችን በጋራ የሚቋደሱበት መጠጦች እየተጎነጩ በድምቅት የሚያከብሩት ነው። 

ለደመራና ለመስቀል እንደ የአካባቢው ወግና ሥርዓት የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ይዘጋጃሉ፤ ለአብነትም በጉራጌ ሕዝብ ዘንድ መስቀልና ክትፎ ያላቸውን ባህላዊ ትስስር ማንሳት ይቻላል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በወለጋና አካባቢው አንጮቴና ጩምቦ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ለመስቀል በተለያየ መልክ ተሰናድተው ለምግብነት የሚቀርቡ ባህላዊ ምግቦች ናቸው። አንጮቴ እንደ ድንችና ሌሎች የሥራስር አትክልት ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ ወጥቶ በተለያዩ ዓይነት ተዘጋጅቶ በአዘቦቱ ቀን ለክብር እንግዳ፤ እንደመስቀል ላሉ ክብረ-በዓላት ደግሞ ከቤተሰብ፣ ዘመድ ወዳጅ በአብሮነት የሚቋደሰው ባህላዊ ምግብ ነው። 

በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ጩምቦ ወይም 'ጮሮርሳ' በሚል ስያሜ የሚታወቀው ባህላዊ ምግብ ደግሞ ከአፍለኛ የቀይ ጤፍ በልዩ የአዘገጃጀት ሥርዓት ተዘጋጅቶ በተነጠረና ለሰውነት ተስማሚ በሆነ ለጋ ቅቤ የሚዘጋጅ ሲሆን በአዘቦቱ ቀን ለክብር እንግዳ፤ እንደ መስቀል ላሉ ክብረ-በዓላት ደግሞ ማህበረሰቡ ተጠራርቶ በአብሮነት የሚቋደሰው ነው።

ወይዘሮ አጌ መንግሥቱ  በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የኦሮሞን ባህላዊ ምግቦች አሰናድተው ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በአካባቢው ባህል፣ ወግና ሥርዓት መሰረት የሚያቀርቡ የ'ኬኛ የኦሮሞ ባህላዊ ምግብ ማዕከል' ባለቤት ናቸው። እሳቸው እንዳሉት ለመስቀል በዓል ከሚቀርቡ ባህላዊ ምግቦች አንጮቴ አንዱና ዋነኛው ነው። አንጮቴና መስቀል የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ አጌ ገለጻ አንጮቴን የተለየ የሚያደርገው ምርቱ በወርሃ መስከረም የሚደርስ በመሆኑ ማህበረሰቡ በመስቀል በዓል በጋራ ከሚቋደሰው እሸት አንዱ ስለሆነ  ከደመራና መስቀል ክብረ-በዓላት ጋር የቆየ ባህላዊና ተለምዷዊ ትስስር ያለውና እንደ መስቀል በዓል ሁሉ ክብር የሚሰጠው ባህላዊ ምግብ መሆኑ ነው። አንጮቴ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰው የተጎዳው "ሰውነቱ ቶሎ እንዲጠገን ያደርጋል" ተብሎ ስለሚታመን ለፈውስነት እንዲሁም ለአራሶች ለወገብ መጠገኛነት፣ ገና ምግብ ለሚጀምሩ ጨቅላ ህፃናት ከምጥን እህል ጋር ተሰናድቶ ለዕድገትና ለአጥንት ጥንካሬ በገንቢነቱ ስለሚረዳና  በተለየ ሁኔታ ለምግብነት ስለሚውል ከህብረተሰቡ ጋር ለዘመናት የዘለቀ ትስስር ያለው ባህላዊ ምግብ ነው።

የመስቀል በዓልን በጥጋብ ማሳለፍ ዓመቱ በሙሉ የጥጋብ ዘመን ይሆናል ተብሎ ስለሚታመን በመስቀል በዓል ጠግቦ መብላት በማህበረሰቡ ዘንድ የተለመደ መሆኑን አንስተው፤ያለው ለሌለው በማካፈልም በመጠራራት ጭምር ጩምቦና አንጮቴን የመሳሰሉ ባህላዊ ምግቦችን በጋር በመቋደስ የደመራና መስቀል በዓልን በአብሮነት ያከብራል ይላሉ።

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ወይዘሮ ባጩ ተስፋዬ፣ አንጮቴ ተወዳጅ እና ተዘውታሪ የባህል ምግብ መሆኑና አዘውትረው እንደሚመገቡት ይገልጻሉ። የአንጮቴ ምርት ሳይበላሽ ለሁለት ለሶስት ዓመታት መሬት ውስጥ የመቆየት ባህርይ እንዳለውም ያስረዳሉ።  መሬት ውስጥ ከሁለት ዓመት በላይ የቆየ አንጮቴም "ጉቦ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህ ምርት በማህበረሰቡ ይበልጥ ተፈላጊ ነው ይላሉ።

ወይዘሮ ባጩ አያይዘውም አርሶ አደሩም ሆነ ባለሃብቶች አንጮቴን  በስፋት አልምተው ምርቱ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ እንዲለመድ የማስተዋወቅ ስራ ቢሰራበት አንጮቴ ገበያ ተኮር ከሆኑ ምርቶች አንዱና ዋነኛው ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ይገልጻሉ።

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አሼቴ ግርማ ተወልደው ያደጉት ገጠር ሲሆን፤ አንጮቴን ከመዝራት ጀምሮ በአሰራሩም ያደጉበት ስለሆነ የተለየ ፍቅር እንዳላቸው ያስረዳሉ። አንጮቴን ከገብስና ከአጃ  እህል ጋር ደባልቆ በማስፈጨት ከወተት ጋር አፍልተው ልጆቻቸውን እያጠጡ ማሳደጋቸውንም እንዲሁ። የልጆቻቸው በሽታ መከላከል አቅምና  ጥንካሬም  ከፍተኛ እንደነበረም ያስታውሳሉ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ገለታ በአካባቢያቸው አንጮቴ፣ ጩምቦና ከደመራና መስቀል በዓል ጋር ጠንካራ ትስስር  ያላቸው መሆኑን ያስረዳሉ። በአካባቢው በበዓላት ወቅት የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች የሚዘወተሩ ቢሆንም፤ በመስቀል በዓል ግን እንደ አንጮቴና ጩምቦን በማህበረሰቡ ዘንድ ጥቅም  ላይ የሚውል ባህላዊ ምግብ የለም ይላሉ።

አቶ አንዳርጌ እንዳሉት ጽህፈት ቤቱ እነዚህን ባህላዊ ምግቦች ለማስተዋወቅና ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማትና አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው። የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በአካባቢው በሚከናወኑ ሕዝባዊ ኹነቶች አንጮቴ ዋና ምግብ ሆኖ እንዲቀርብ ዝግጅት ተደርጓል። 

አንጮቴ ድርቅና በሽታን  ተቋቁሞ ጥሩ ምርት የሚሰጥና ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል የምግብ ዓይነት በመሆኑ፤ ይህን ምርት የማላመድና የማስተዋወቁ ስራ ትኩረት እንዲያገኝ በማድረጉ በኩል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም