የኢትዮጵያና ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት በተለያዩ የትብብር መስኮች አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው - አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት በተለያዩ የትብብር መስኮች አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው - አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና ቻይና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በተለያዩ የትብብር መስኮች አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የቻይና ሪፐብሊክ ምስረታ 74ኛ ዓመት ብሔራዊ ቀን ትናንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በመርኃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵና ቻይና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው።
በዚህም ቻይና በኢትዮጵያ የፈጣን መንገድ፣ የባቡር መስመር፣ የኃይል ግንባታና ቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ መስኮች ገንቢ ሚናም እየተጫወተች መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሁለቱን አገራት ስትራቴጂክ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ኢትዮጵያ አበክራ የምትሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ፤ ቻይና በአፍሪካ የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በቀጣይም አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታና የድኅነት ቅነሳ ልምዷን በማጋራት አፍሪካዊያን ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት መስኮች ትብብሯን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሺን ቺንሚን፤ ቻይና የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቪ በመቅረጽ በአፍሪካ በተለያዩ የልማት መስኮች የራሷን አሻራ እያሳረፈች ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ማዕቀፍ 53 ዓመታትን ያሳለፈው የኢትዮ-ቻይና ሁሉን አቀፍና ስትራቴጂክ አጋርነትም በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የቻይና ሪፐብሊክ ብሔራዊ ቀን “ሺዪ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1949 የቀድሞው የቻይና ፕሬዝዳንት ማኦ ዘዶንግ ሕዝባዊ መንግሥት መመሥረቱን ተከትሎ በየዓመቱ የሚከበር ብሔራዊ በዓል ነው።