ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

88

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2016 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንኳን ለ2016 ዓ.ም የደመራ እና የመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፣ “መስቀል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለምንም ልዩነት እስከ መሰቀል እና ሞት ድረስ ራሱን አሳልፎ የሰጠበት ተወዳዳሪ የማይገኝለት ፍቅር መገለጫ ነው” ብለዋል።

“እኛም በመስቀሉ ላይ የተገለጠው የክርስቶስ የቤዛነት፣ የፍቅር እና እውነት መጠን፣ እርስ በእርስ በመዋደድ እና በመትጋት ከማይረቡ ጉዳዮች፣ እርስ በእርሳችን ከሚጋጩ እና ከሚያጠራጥሩን ሐሳቦች እና ድርጊቶች ርቀን በፍቅር፣ በአንድነት በመኖር እንደ ደመራ አሰባሳቢ ጥበብን እየገበየን፣ በዓመት አንዴ ደመራን ስናከብር ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ በተግባር እውነተኛ የመስቀሉ ወዳጆች መሆናችን በፍቅራችን እየገለጽን መኖር ይገባናል” ሲሉም አክለዋል።

ሁላችንም ለከተማችን እና ለሀገራችን ሰላም እና ልማት ደመራችንን እንደምር ያሉት ከንቲባዋ፣ በዓሉ የፍቅር፣ የሰላም፣ የጤና እና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም