በሻምፒዮናው ለሀገራችን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል - አትሌቶች - ኢዜአ አማርኛ
በሻምፒዮናው ለሀገራችን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል - አትሌቶች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2016(ኢዜአ)፦ በላቲቪያ ሪጋ በሚካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችላቸውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ኢዜአ ያነጋራቸው በሻምፒዮናው ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ገለጹ።
በሻምፒዮናው ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን አሸኛኘት ተደርጎለታል።
በሽኝት መርሐ-ግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አትሌቶች በውድድሩ የተሻለ ውጤት ለማግኘትና የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርጎ ለማውለብለብ በጽናት መታገል እንዳለባቸው አምባሳደር መስፍን ገልጸዋል።
በውድድሩ ለሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድንም የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ አትሌቶቹ የአየር ንብረቱንና ሌሎች ጫናዎችን ተቋቁመው በውድድሩ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ፌዴሬሽኑ ለአትሌቶቹ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በሴቶች ግማሽ ማራቶን የምትሳተፈው አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ፤ አትሌቶቹ ውድድሩ በሚካሄድበት ስፍራ ካለው ሞቃታማ የአየር ንብረት ጋር የሚጣጣም ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጻለች።
በውድድሩም የተሻለ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀቷን ተናግራለች።
በወንዶች ግማሽ ማራቶን የሚሳተፈው አትሌት ጀማል ይመር በበኩሉ፤ የአትሌቶች የመሰባሰቢያ ጊዜና ዝግጅት አጭር ቢሆንም የአየር ንብረቱን ተቋቁመው በቡድን ስራ ጥሩ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀታቸውን ገልጿል።
በግማሽ ማራቶን የሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን አሰልጣኝ ጌታመሳይ ሞላ፤ አትሌቶቹ ለሶስት ሳምንታት መዘጋጀታቸውንና ከሞቃታማ የአየር ንብረት ጋር በሚቀራረቡ ቦታዎች ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
የዝግጅት ጊዜው አጭር ቢሆንም በሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀታቸውንም ነው አሰልጣኙ የገለጹት።
የመጀመሪያው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና የፊታችን እሁድ መስከረም 20/2016 በላቲቪያ ሪጋ ይካሄዳል።
በሻምፒዮናው ከ57 አገራት የተውጣጡ 347 አትሌቶች ይሳተፋሉ።
1 ማይል፣5 ኪሎ ሜትር እና የግማሽ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ውድድር የሚካሄድባቸው ርቀቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ7 ሴቶች እና በ6 ወንዶች በድምሩ በ13 አትሌቶች ትወከላለች።