ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን የአመራርነት ሚና ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/ 2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን የአመራርነት ሚና ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን  ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገለጸ። 

በመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከግንባር ቀደም ሰላም አስከባሪ አገራት ውስጥ አንዷ ነች።

የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከጥንት ከኮሪያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የጀመረና ዘመናትን ተሻጋሪ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁንም በላቀ መልኩ መቀጠሉን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሰላም እጦት ባለባቸው አጎራባች አገራት ወታደሮቿን በማሰማራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን በመወጣት ከፍተኛ ድርሻ በማበርከት ታሪኳን እያስቀጠለች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ዘመቻ የምታደርገው ተሳትፎም ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ደምቃ እንድትጓዝ ማስቻሉን ገልጸው በቀጣይም የሠራዊቱን ብቃትና ዝግጅት በማጎልበት ተሳትፎውን  ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

የሰላም ማስከበር ግጭት አፈታትና የአስተዳደር ውጤታማነትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸው ጎን ለጎንም ከፍተኛ መኮንኖችን በከፍተኛ ትምህርት የማብቃት ሥራም ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።   

የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደመቀ መንግሥቱ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በቀጣናው የተወጣችው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ ከበሬታ አስገኝቶላታል ብለዋል።

በዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማት ውስጥ ያላት የአመራር ውክልና ግን በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግዳጅ አፈጻጸም ካስገኘችው ከበሬታ አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።  

የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ የአመራር ቦታዎችም የሰላምና ግጭት አፈታት የእውቀትና የትምህርት ዝግጅቶችን በቀጥታና ተዘዋዋሪ የሚጠይቁ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ተቋማት የአመራር ቦታ ድርሻ ለማሳደግ በሰላምና ግጭት አፈታት የትኩረት መስክ ብቃት ያላቸው ወታደራዊ መኮንኖችን ለማፍራት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱም በሰላም ምንነት፣ በግጭት አፈታት፣ ድኅረ-ግጭትና መልሶ ማቋቋም የትምህርት መስኮች ላይ ብቁ መኮንኖችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም