ለሰባት ዓመታት ደርቆ የነበረው የጨርጨር ሃይቅ ተመልሶ ወደ ቱሪዝም መስህብነት እየተቀየረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሰባት ዓመታት ደርቆ የነበረው የጨርጨር ሃይቅ ተመልሶ ወደ ቱሪዝም መስህብነት እየተቀየረ ነው

ጭሮ፤ መስከረም 15/2016 (ኢዜአ)፡- ለሰባት ዓመታት ደርቆ የነበረው የጨርጨር ሃይቅ ተመልሶ ወደ ቱሪዝም መስህብነት እየተቀየረ መሆኑን የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የጨርጨር ሃይቅ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሀብሮ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ቦኬና ኦዳ ቡልቱም ወረዳዎችንም ያዋስናቸዋል፡፡
634 ሔክታር መሬት የሚሸፍነው የጨርጨር ሀይቅ ልክ እንደ ሃረማያ ሃይቅ ደርቆ ለሰባት ዓመታት ቢቆይም በአካባቢው በተሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ እና በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ውጤታማነት ዳግም ነፍስ ዘርቶ የአሳ ምርት እስከ መስጠት ደርሷል፡፡
በሀይቁ ዙሪያ የሚኖሩ የሶስቱም ወረዳዎች ነዋሪዎች የተፋሰስ ልማት ስራዎችንና በአዋሳኞቹ እርከኖችን በመስራት እንደዚሁም ዛፎችን በመትከል የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ይዘት መመለስ በመቻላቸው ሃይቁ እንደገና እንዲያገግም ረድቷል፡፡
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቱሪዝም ፕሮሞሽንና ገበያ ልማት ባለሙያ አቶ አብዱ ሙሳ በሰጡት አስትያየት በአሁኑ ወቅት የሃይቁ የውሃ ይዘት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።
ይህን ተከትሎም ሃይቁን በሚያዋስኑት ሶስት ወረዳዎች ያሉ ወጣቶች በአሳ ምርት ተደራጅተው ውጤታማ መሆን ችለዋል ብለዋል፡፡
ከሶስት ዓመታት ወዲህ እንደገና ነፍስ ዘርቶ የድሮ ውበቱ የተመለሰው ሃይቁ ለብዙ ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ሌላ በአካባቢው ጎብኚዎችን እስከ መሳብ ደርሷል ብለዋል፡፡
እስከ አሁን ሶስት የአሳ አምራች ማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ እንደሚገኙና እስከ አዲስ አበባ ድረስ በአሳ ሽያጭ ተጠቃቀሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በሃይቁ ዙሪያ አርሶ አደሮች የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችንም በስፋት እያመረቱ ገቢያቸውን በማሳደግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የሃይቁ ገጽታና የአሳ ምርቱ ላይ ተፅዕኖ እያመጣ ያለውን የእምቦጭ አረም ማህበረሰቡ በርብርብ በማጽዳቱ ለውጥ እየታየ መምጣቱንም አቶ አብዱ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከሃይቁ የሚገኘውን ፋይዳ በመረዳት የአካባቢው ህብረተሰብ ሃይቁን ከእምቦጭ አረም በማጽዳትም ሆነ ሁለንተናዊ እንክብካቤ ለመቀጠል ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡
በሃይቁ ዙሪያ የተለያዩ የባህል እቃ መሸጫዎች እንዲኖሩ በማድረግ ከቱሪዝም መስህቦች አንዱ እንዲሆን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የጨርጨር ሃይቅ የሚገኝበት ሃብሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሐሰን መሐመድ ሃይቁ ለዘመናት ለአካባቢው ማህበረሰብ የመኖር ህልውና የነበረና በመሃል ደርቆ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሐሰን ሃይቁን ለቱሪዝም መስህብነት ለመጠቀም የመጀመሪያው የአካባቢውን ማህበረሰብ አመለካከት መለወጥ ላይ እየሰሩ መሆኑንና ሁሉም አካባቢውን የመንባከብና የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ ማድረጋቸውንም አክለዋል፡፡
በሃይቁ ዙሪያ ከሚገኙት ሌላኛው የኦዳ ቡልቱም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሃሚድ ኢብራሂም በበኩላቸው ወጣቶችንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ሰብስበን የእምቦጭ አረም ከላዩ በማንሳት ሃይቁ ጤናማ ገጽታውን ጠብቆ እንዲቆይ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለንም ብለዋል፡፡
የሃይቁን ደረጃ ከፍ በማድረግ በቱሪዝም ተጠቃሚ መሆን በምንችልበት አግባብ ላይም እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ከመስከረም 13 እስከ ዛሬ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም በልዩ ልዩ ስርዓቶች እየተካሄደ ባለው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ውስጥ ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል የቱሪዝም መስህቦችን ማልማትና ማስተዋወቅ ዋነኞቹ ናቸው።
እንደ ሃረመያ እና ጨርጨር ጠፍተው የተመለሱ ሃይቆችንም ሆነ ያሉትን በአግባቡ አልምቶና አስተዋውቆ ከዘርፉ የቱሪዝም ገቢ ማመንጨት ማስቻል በክልሉ መንግስት ትኩረት ካገኙ ተግባራት መካከል መሆኑም ይታወቃል።