ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ እና የመውሊድ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ በቂ ዝግጅት ተደርጓል-የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15/2016 (ኢዜአ):-የመስቀል ደመራ እና የመውሊድ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ።

ግብረ-ሃይሉ በላከው መግለጫ፤ ለመላው ሕዝበ ክርሰቲያንና ለመላው ሕዝበ ሙስሊም እንኳን ለመስቀል ደመራና ለመውሊድ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።

ሁለቱም በዓላት ሀይማኖታዊ ሥርዓታቸው በሚፈቅደው መሠረት በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲጠናቀቁ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሰላም ወዳዱ ኅብረተሰብ ጋር በመተባበር በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱንም የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገልጿል።

በሃይማኖት ሽፋን እኩይ የፖለቲካ አጀንዳዎቻቸውን ለማራመድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተገቢ እንዳልሆኑ ሁሉም ተገንዝቦ ከበዓላቱ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ውጪ ግጭትና ሁከት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በባነር፣ በአልባሳት እንዲሁም እንደ ርችት የመሳሰሉ ተቀጣጣይ ነገሮችን፣ ስለታማና የጦር መሳሪያ በማንኛውም ሁኔታ በዓላቱ ወደ ሚከበሩባቸው ቦታዎች ይዞ መግባት በጥብቅ መከልከሉን አስታውቋል።

ክልከላውን ተላልፈው የበዓላቱን ድባብ ለማደብዘዝ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይም ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ከወዲሁ ገልጿል።

በዓላቱ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲጠናቀቁ የጋራ ግብረ-ኃይሉ በቂ ዝግጅት አድርጓል ሲል የገለጸው የጋራ ግብረሃይሉ ኅብረተሰቡም ለፀጥታ ኃይሉ አጋዥና ተባባሪ በመሆን የድርሻውን እንዲወጣ አሳስቧል።

በበዓላቱ ድባብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች፣ በዓሉን በኮሚቴነት የምታስተባብሩና የምትመሩ አካላት፣ ሕዝበ ክርስቲያን እና ሕዝበ ሙስሊሙ ከፀጥታ አካላት የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓላቱ በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲጠናቀቁ ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉ ሲል የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ህብረተሰቡ በዓላቱን የሚያውኩ የተለዩ እንቅስቃሴዎችን በአቅራቢያ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በመጠቆም ሰላምና ደኅንነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ላይ አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በላከው መግለጫ ጥሪውን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም