ኢትዮ-ቴሌኮም እና የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የስማርት የእሳትና አደጋ ስጋት አመራር ትግበራ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/ 2016 (ኢዜአ)፦  ኢትዮ-ቴሌኮም እና የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የስማርት የእሳትና አደጋ ስጋት አመራር ትግበራ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ ፈጣን የአደጋ መረጃ እና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን ለማጎልበት የሚያግዝ ነው፡፡

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ እና የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ቴክኖሎጂ ኦፊሰር ታሪኩ ደምሴ ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የተቀናጀ የግንኙነት እንዲሁም የመረጃ ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የአደጋ ስራ አመራር አገልግሎቶችን ለማዘመን ይሰራል፡፡

በዚህም ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊና በቀላሉ ተደራሽ የሚሆን የአደጋ ጊዜ የጥሪ ማዕከል በማዘጋጀት  አገልግሎቱን በጥራትና በቅልጥፍና እንደሚያቀርብ ተመላክቷል።

በተጨማሪም የተቀናጀ የድንገተኛ አደጋ ጊዜ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ ስርዓት አቅርቦት እና የተከላ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ስልጠና እና ድጋፍ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ ስምምነቱ የእሳትና አደጋ ስጋት አመራርን በተሻለ መልኩ ለመምራት ያግዛል ብለዋል።

ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከልና በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ወሳኝ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።

በስምምነቱ መሰረት በቀጣዮቹ አራት ወራት ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ቴክኖሎጂ ኦፊሰር ታሪኩ ደምሴ በበኩላቸው ኩባንያው ዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራእይ ለማሳካት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በዚህም ለተለያዩ ተቋማት የቴክኖሎጂ እና ዲጂታል አማራጮችን በማቅረብ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያዘምኑ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው ስምምነትም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ስምምነቱም የዜጎችን የእለት ተእለት እንቅስቃሴን በማሳለጥ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው አመላክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ይክፈለው ወልደመስቀል፤ ኮሚሽኑ ላለፉት 90 አመታት የእሳት አደጋ ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ስምምነቱ  ከተማዋን የሚመጥን አገልግሎት  ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም