ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ የመስቀል ደመራ በዓልን ሲያከብር አብሮነትን በሚያጠናከር መልኩ ሊሆን ይገባል--አቶ ጥራቱ በየነ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2016 (ኢዜአ)፦በመዲናዋ የመስቀል ደመራ በዓል ሲከበር አብሮነትን በሚያጠናከር መልኩ መሆን እንዳለበት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ገለጹ፡፡

በነገው ዕለት የሚከበረውን የደመራ በዓል ምክንያት በማድረግ የሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች በመስቀል አደባባይ የጽዳት መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ፣ የጽዳት ዘመቻው ቦታውን ለክብረ በዓሉ ምቹ ከማድረግ ባሻገር የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች አብሮነታቸውን ያሳዩበት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በቋንቋ፣ በሃይማኖት ብዝኃ ማንነት ቢኖራቸውም እርስ በርስ በመደጋገፍ ጠንካራ መስተጋብር  እንዳላቸው ገልጸዋል።

በተለይ የሃይማኖት በዓላት በሚከበሩበት ወቅት አንዱ የሌላውን በዓል በሰላምና በድምቀት እንዲከበር የሚያደርጉት ትብብር ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ እሴት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ይህን የአብሮነትና እርስ በርስ የመደጋገፍ በጎ እሴትን ማጠናከር ተገቢ  ነው ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ሰላምና አንድነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲከበር የመዲናዋ ነዋሪዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ስራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን በበኩላቸው፤ የበዓሉን ማክበሪያ ስፍራ ምቹ ለማድረግ በጽዳት ዘመቻው ለተሳተፉ ወገኖች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የመስቀል በዓልን ስናከብር ክርስቶስ ለሰው ልጅ የከፈለውን ዋጋ እና የአርዓያነት ተግባር በማስታወስ፣ ለሌሎች በጎ በማሰብ እና አቅመ ደካሞችን በማገዝ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የእስልምና ሃይማኖት ተወካይ የሆኑት ቢላል ሙሔ የመስቀል ደመራ በዓል ማክበሪያ ስፍራውን በማፅዳት ስራ በመሳተፋቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም አብሮነትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ለዘመናት አብረው መኖራቸውን በመጥቀስ፤ ይህን አንድነት ማጠናከርና እርሰ በርስ መተጋገዝን ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትየጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ተወካይ ፓስተር ጌትነት ለማ በበኩላቸው፤ የመስቀል ደመራ በዓል የወንድማማችነት እሴትን በሚያጎላ መልኩ እንዲከበር በጽዳት ዘመቻው መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም