ኢትዮጵያና አልጄሪያ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር የሚያሸጋግሩበት ምዕራፍ ላይ ናቸው- አምባሳደር ሞሃመድ ላምኔ ላበስ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/ 2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና አልጄሪያ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር የሚያሸጋግሩበት ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር ሞሃመድ ላምኔ ላባስ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር ሞሃመድ ላምኔ ላባስ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ሁለቱ ሀገራት ረዥም  ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና አልጄሪያ በፖለቲካው መስክ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ቢሆንም፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ  በሚጠበቀው ልክ ትስስር  ሳይፈጠር መቆየቱን አንስተዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የቀጥታ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሳይጀመር መቆየቱ ለኢኮኖሚያዊ ትብብሩ አለመጠናከር አንደኛው ምክንያት እንደነበርም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

ይህን ለማሻሻል በአልጀርስና በአዲስ አበባ መካከል ቀጥታ የአየር በረራ አገልግሎት መጀመር ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ትብብርን ለማጠናከር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የአልጄሪያ አየር መንገድ ባሳለፍነው ሳምንት ከአልጄርስ-አዲስ አበባ የቀጥታ በረራ መጀመሩን  ገልጸዋል።

ይህም የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በማጠናከር ወደላቀ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሸጋገር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።

በአቪየሽን ዘርፉ የተጀመረው ትብብርም አልጄሪያ የአፍሪካ ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙ ልምድ እንድትቀስም የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ትብብሩን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በነሐሴ 2014 ዓ.ም በአልጄሪያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት አብዱልመጅድ ታቡኔ ጋር የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጎልበት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።

 

መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል የቀጥታ በረራ ማስጀመር፤ የንግድ ልውውጡንና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸው አይዘነጋም።

 

አልጀሪያ እ.ኤ.አ 1962 ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረቱ ሲሆን፤ አልጄሪያ ኤምባሲዋን እ.ኤ.አ በ1976 በአዲስ አበባ ከፍታለች።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም