ኀብረተሰቡ የበዓል ወቅት ግርግርን ተጠቅመው በሀሰተኛ የብር ኖት ግብይት ከሚፈጽሙ አጭበርባሪዎች ሊጠነቀቅ ይገባል - ብሔራዊ ባንክ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2016 (ኢዜአ)፡-ኀብረተሰቡ የበዓል ወቅት ግርግርን ተጠቅመው በሀሰተኛ የብር ኖት ግብይት ከሚፈጽሙ አጭበርባሪዎች ሊጠነቀቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስገነዘበ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በበዓላት ወቅት የሚፈጸሙ ግብይቶች ጥድፊያና ግርግር የሚበዛባቸው በመሆኑ ወንጀለኞች ለማጭበርበር ስራቸው እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀሙበት አመላክቷል፡፡

ከዚህ አኳያ በቀጣይ ቀናት የሚከበሩ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ በሚፈጸሙ ግብይቶች ላይ ወንጀለኞች በስፋት ሊሳተፉ እንደሚችሉም ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም ኀብረተሰቡ የበዓሉን ግርግር ተጠቅመው ሀሰተኛ የብር ኖት በማሳተም ግብይት ከሚፈፅሙ ወንጀለኞች ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

የገንዘብ ኖቶች ላይ ያሉ የደህንነት ምልክቶችን በጥንቃቄ በመመልከት ግብይት መፈጸም እንደሚገባም ባንኩ አሳስቧል፡፡

ሕብረተሰቡ ሀሰተኛ የብር ኖት የሚያትሙ፣ የሚያዘዋውሩ፣ ብሎም ለገበያ የሚያቀርቡ ወንጀለኞችን ለጸጥታ ኃይሎች በመጠቆም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም