የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ ፣ የመውሊድና የመስቀል በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት ተደርጓል- ኮማንድ ፖስቱ - ኢዜአ አማርኛ
የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ ፣ የመውሊድና የመስቀል በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት ተደርጓል- ኮማንድ ፖስቱ

ደሴ፤ መስከረም 15/2016 (ኢዜአ)፡- የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ ፣ የመውሊድና የመስቀል በዓላት በሰላማዊ መንገድ እንዲከበሩ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡
የኮማንድ ፖስቱ አባል ሻለቃ ደግሰው ዶሻ እንደገለጹት፤ መስከረም 21 የሚከበረውን የግሸን ደብረ ከረቤ የንግስ በዓል በሰላም እንዲከበር ማህበረሰቡን በማሳተፍ ተገቢው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
ምዕምናኑ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዓመታዊ በዓሉን ያለ ስጋት ማክበር እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።
ህብረተሰቡ ለሰላም ባለው ብርቱ ፍላጎትና ትብብር አካባቢውን ሰላም ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህንን ዘላቂ ለማድረግ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል፡፡
የመውሊድ፣ የመስቀልና ደመራ በዓላትም እንዲሁ በሰላም እንዲከበሩ ተገቢውን ስምሪት በመስጠት ቅደመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
በዓላቱ በሰላምና በአንድነት እንዲከበሩ የጸጥታ መዋቅሩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ቅደመ ዝግጅት አድርጓል ያሉት ሌላው የኮማንድ ፖስቱ አባል ሻለቃ መላኩ ቶላ ናቸው፡፡
ሰራዊቱ የሀገርና የህዝብን ደህንነት በመጠበቅ የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ማንኛውንም መስዋትነት እየከፈለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡም ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጠል ጠይቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ እያሱ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓልን ለማክበር ወደ ስፍራው የሚመጡ እንግዶችን በተገቢው ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ከህብረተሰቡና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለአንግዶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የመንገድ ጠረጋ፣ የውሃ፣ የመብራትና ሌሎችንም አገልግሎት መስጫዎች መመቻቸታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዓሉን ምክንያት በማድረግ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ጭምር በማድረግ ለገቢ ምንጭነት እንዲውልም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የትራንስፖርት ችግር እንዳይኖር ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነውም ብለዋል።
በግሸን ደብረ ከረቤ የንግስ በዓል ላይ ከአንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በየዓመቱ መስከረም 21 በድምቀት የሚከበረው የግሸን ደብረ ከረቤ የንግስ በዓል በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ውስጥ መሆኑ ይታወቃል።