የመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጊድ በነገው ዕለት በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል-የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጊድ በነገው ዕለት በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል-የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤መስከረም 15/2016(ኢዜአ)፡-1ሺህ 498ኛው የነብዩ ሙሀመድ የመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጊድ ነገ እንደሚከበር የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ በዓሉን በተለያዩ ኃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ሲያካሄድ መቆየቱን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ አባል ሸህ አቡዱል ሂሚድ አህመድ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ሙሰሊሙ የነብዩ መሀመድን ልደት የሚያከብረው የእሳቸውን የደግነት ሥራዎች ተግባራዊ ለማድረግና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
1ሺህ 498ኛው የነብዩ ሙሀመድ ልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ከታላቁ የአንዋር መስጂድ ወጣት ጀምዓ ጋር፣ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የተለያዩ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር የቅደመ ዝግጅት ስራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም በዓሉ የሚከበርበትን ቦታ የማጽዳትና የማስተካከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"ነብዩ ሙሃመድ ለዓለም እዝነትና ደግነትን ያስተማሩ እንደመሆናቸው እኛም ተከታዮቻቸው ለሌሎች ወገኖቻችን እዝነትንና ደግነትን በማሳየት አርአያነታቸውን ልንከተል ይገባል" ብለዋል
የነብዩ መውሊድ በዓል ሲከበር ደግ ሥራዎቻቸውንና እዝነቶችን ተግባራዊ በማድረግ መሆን እንዳለበትም ነው የገለጹት።
በዝግጁትም ላይ የአንዋር መስጊድ ወጣት ጀመዓ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች የተለያዩ እምነት አባቶችና ምዕመናን ተገኝተዋል።