ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ፣የመውሊድና የኢሬቻ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ አስፈላጊው የጋራ ዝግጅት ተደርጓል - በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 14/2016 (ኢዜአ)፦ የመስቀል ደመራ፣የመውሊድና የኢሬቻ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ አስፈላጊው የጋራ ዝግጅት  መደረጉን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የተለያዩ  ተቋማት አስታወቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ፣ የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የበዓላቱን ዝግጅት በተመለከተ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን  መግለጫ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ይክፈለኝ ወልደ መስቀል፤ የደመራ በዓል በሚከበርባቸው አከባቢዎች ድንገተኛ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የመስቀል በዓልን ጨምሮ በመዲናዋ የሚከበሩ በዓላት ድንገተኛ አደጋ እንዳይከሰትባቸው የጥንቃቄ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ድንገተኛ አደጋዎች ከተከሰቱም ፈጥኖ መድረስ የሚችሉ የአደጋ መከላከል ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ቦታዎች ዝግጁ ሆነው እንዲቆሙ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ገበየሁ ሊካሳ በበኩላቸው  ከበዓላቱ ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የደመራ በዓል በሚከበርባቸው አካባቢዎች ላይ እንዲሁም በመዲናዋ አምስቱ መግቢያ በሮች ላይ የመንገድ መብራት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የውሃ ስርጭት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ሞገስ አርጋው ናቸው።

በዓላቱን የሚያከብሩ ዜጎች በተለያዩ ስፍራዎች የውሃ አቅርቦት እንዲያገኙ የቦቴ ተሽከርካሪዎች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም