ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አምራቾችና አቅራቢዎች ጋር የገበያ ትስስርን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 14/2016 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አምራቾችና አቅራቢዎች ጋር የገበያ ትስስርን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የተዘጋጀው ሶስተኛው ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አቅራቢዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በጉባኤው በርካታ ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አቅራቢዎችና ባለድርሻዎች በአካል በመገኘት እንዲሁም በበይነ-መረብ ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ የጉባኤው መካሄድ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አቅራቢዎችና አምራቾች ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ የሚያስችል ወሳኝ ጉባኤ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት ስርዓት የማዘመንና የማሻሻል ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው የመድሃኒት አቅርቦት አማራጮች እንዲሰፉ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅስዋል።

ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አምራቾችና አቅራቢዎች ጋር የገበያ ትስስርን የሚያጠናክሩ ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ ለሚሹ የውጭና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችም ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የግዥ አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ፤ የመድሃኒት አቅርቦትና ግዥ ስርዓት ዘመናዊ አሰራርን የሚጠይቅ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በመሆኑም እንደ ሀገር የተጀመረውን ዘርፉን የማዘመንና የማስፋት እቅድ ለማሳካት ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው የዛሬው መድረክም የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

ከ75 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጰያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በሀገሪቷ 83 በመቶ የሚሆነውን የመድሃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም