ቀጥታ፡

መንግስት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር የተቋማትን የማስፈጸም አቅም በማጎልበት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መስራት አለበት- ምሁራን

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 14/2016 (ኢዜአ)፦መንግስት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር የተቋማትን የማስፈጸም አቅም በማጎልበት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መስራት እንዳለበት የምጣኔ ሀብትና የአስተዳደር ጉዳዮች ምሁራን ገለጹ።

በኢትዮጵያ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የባንክና ፋይናንስ ጥናት ክፍል አስተባባሪና ፋይናንሻል ኢኮኖሚስት ተወልደ ግርማ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፥ የወጪና ገቢ ምርት አለመጣጣም፣ የንግድ ሚዛን መዛባት፣ የተቋማት የገበያ አሰራር የማስፈጸም አቅም ማነስ ዋነኛ የኑሮ ውድነት ምንጮች ናቸው። 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የገቢ ምርት ጥገኛ መሆኑን ያነሱት ምሁሩ፤ በወጪና ገቢ ምርቶች ያለው የምጥጥን ጉድለትም ዜጎች ለኑሮ ውድነት መባባስ እንዲጋለጡ ማድረጉን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የሰላምና ፀጥታ መደፍረሶች በምርታማነት ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ጫና እንዳለ ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ተለዋዋጭነትና በየጊዜው መጨመር፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትም ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት የሚፈጠረው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በወርሃዊ ገቢ የሚተዳደርና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍልን እየፈተነ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት።

በመሆኑም መንግስት የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የግብርና፣ የኢንዱስትሪና ሌሎች የልማት ዘርፎችን ምርታማነት በማሳደግ የአገር ውስጥ ፍጆታን በራስ አቅም መሸፈን እና የገቢና ወጪ ምርቶችን የማመጣጠን ስራም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ መደፍረስን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት በግጭት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን  ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት ማስገባትም የመንግስት የአዲሱ ዓመት ቁልፍ ስራው እንዲሆን ጠይቀዋል።

ከዚህም ባለፈ  የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የመንግስት ተቋማት የገበያ ስርዓቱ ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር የማድረግና የማስፈጸም አቅማቸውን ማጎልበት ተገቢ ነው ብለዋል።

በከተሞች አካባቢ የዋጋ ንረትን ለማርገብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋትን ጨምሮ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው የጠቆሙት።

በኢንስቲትዩቱ የተቋማት ግንባታ እና አስተዳደር ፖሊሲ ማዕከል አስተባበሪ ዶክተር ግርማ ተሾመ በበኩላቸው፥ ብልሹ አሰራርና ሙስና በዜጎች የእለት ተእለት ኑሮ ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን  አስረድተዋል።

በመሆኑም ተቋማዊ አደረጃጀት እና የአሰራር ውስንነቶችን ፈትሾ የማስፈጸም አቅምን ከማጎልበት ጎን ለጎን ሌብነት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባም  ጠቁመዋል።

የመንግስት ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን የማስፈጸም አቅም ለማሻሻልም ስልጠና እና የቴክኖሎጂ አሰራርን ማስፋት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም