የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው የልማት ድርጅቶች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዘገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው የልማት ድርጅቶች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዘገቡ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 14/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው የልማት ድርጅቶች በ2015 ዓ.ም ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገባቸውን ይፋ አደረገ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሀብረቢ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በ2015 ዓ.ም የሚያስተዳድራቸው የልማት ድርጅቶች የነበራቸውን የስራ እንቅስቃሴ አብራርተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት አብዛኛዎቹ የልማት ድርጅቶች በዕዳ የተዘፈቁ፣ ከኪሳራ ያልተላቀቁና የፋይናንስ አስተዳደራቸውም በውስብስብ ችግር ውስጥ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ለውጡን ተከትሎ ግን መንግስት በወሰደው ውሳኔ የተከማቸ እዳቸውን የማቃለል፣ የድርጅቶቹን የፋይናንስ አስተዳደር በማሻሻል ትርፋማ የቢዝነስ አካሄድ እንዲከተሉ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በዚህ ሂደትም 27 የልማት ድርጅቶችን በአንድ ጥላ ስር የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ መመስረቱን ነው ያነሱት።
የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ቁመናቸው እንዲስተካከል መደረጉን ገልጸው፤ ፈሰስ የተደረገባቸውን ሀብት ውጤታማ በማድረግ ልማትን እንዲያፋጥኑ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲሰማሩ እየተደረገ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በዚህም ከ27ቱ የልማት ድርጅቶች መካከል በርካቶቹን ወደ አትራፊነት ማሸጋገር ተችሏል ነው ያሉት
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር ያሉ የልማት ድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት አሁን ላይ ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በ2015 ዓ.ም ድርጅቶቹ ከ900 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ ማግኘታቸውን አንስተው ከዚህም ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ተመዝግብል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ችግር ያለባቸው ድርጅቶች ጥቂት መሆናቸውን ጠቅሰው በተያዘው በጀት ዓመት መሰረታዊ ችግራቸው ተወግዶ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ድርሻ እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የንግድና ኢንቨስትመንት ፍላጎት ለማሟላት በመንግስት የተቋቋመ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።