ከገበታ ወደ ገበያ

(ሰለሞን ተሰራ)

ኢትዮጵያ ከ10 ሺ ዓመታት በፊት ከኒዮሊቲክ አብዮት ዘመን ጀምሮ የበርካታ አዝእርትና እንስሳት ሀብት መፍለቂያ ሆና ዛሬ ላይ ደርሳለች።

ከዚያ ዘመን ጀምሮ የአገራችን ገበሬ በስራ ያካበተውንና በተፈጥሮ የተሰጠውን ችሎታ በመጠቀም ዘመናዊና ቴክኖሎጂ በወለዳቸው መሳሪያዎች ሳይታገዝ፣ በየጊዜው የአፈሩ ለምነት እየቀነሰ ከሄደው መሬትና ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ጋር እየታገለ ቁጥሩ እየናረ የሚሄደውን ህብረተሰብ ከመመገብ ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም።

ግብርናው ከቀደሙት ጊዜያት በተለየ ሁኔታ ትኩረት ባገኘበት በዚህ ዘመንም ከተደቀኑበት እጅ ጠምዛዥ ጉዳዮች ጋር ግብግብ ውስጥ ነው። 

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድርቅ፣ የፖለቲካና የገበያ አለመረጋጋት፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ውስንነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ የዘርፉ ኢንቨስትመንት አለመዳበር የዘርፉ ተግዳሮት ሆነው ቀጥለዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በ78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ባደረጉት ንግግር በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽእኖ በሚገባ አመላክተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በተለይ በአፍሪካና በሌሎች በማደግ ላይ ያሉ አገራት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ቀውስ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ እንዲበጅ እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።

በተለይ ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ ጫፍ እየተሳተፉበት ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የዚህ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል። 

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ላለፉት ተከታታይ አራት ዓመታት በሰራችው ስራ በአካባቢ ጥበቃና በግብርናው ዘርፍም ውጤት ማግኘቷ እሙን ነው።

ነገር ግን ፈተናዎቹን በድል ለመሻገር የሚደረጉ ጥረቶችና በዘርፉ የተገኙ አበረታች ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ሃይል፣ በተደራጀ የግብርና መሳሪያና ማቀነባበሪያ በመደገፍ አገርና ህዝብ ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ለማስቻል ብዙ መስራት ይጠይቃል።

በተለይ የግብርና ሜካናይዜሽንን ከማስፋፋትና ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ከማቅረብ አኳያ መንግስት እየሰጠ ያለው ትኩረት የበለጠ መጠናከርና ማደግ ይኖርበታል።

የግብርናና የገጠር ልማት የፋይናንስና ብድር አቅርቦትን ማጠናከር እንዲሁም የአካባቢና ስነ ምህዳር ጥበቃ ስራዎችን በዘላቂነት መተግበር ያሻል።

በተለይ ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት እየሰራችበት ያለውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ጉዳይ ከዚህ ቀደም የነበረውን የግብርና አሰራር በመቀየርና አማራጮችን በማማተር እውን ማድረግ ይጠይቃል። 

ኢትዮጵያ በዝናብ ወይም በመስኖ መልማት የሚችል ያልተነካ ሰፊ መሬት እንዳላት የሚታወቅ ሲሆን ይህን ያልታረሰ መሬት በአግባቡ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አንዱ አማራጭ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግብርናው ከ34 በመቶ በላይ የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ ይዟል፡፡

በተጨማሪም ዘርፉ 79 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች መተዳደሪያ ሲሆን በተመሳሳይ 79 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ንግድ ገቢ በመሸፈንና ለአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትና ገበያ የጥሬ እቃ አቅራቢ በመሆንም ይታወቃል።

መንግስት በግብርናው ዘርፍ የወሰዳቸው የሪፎርም ስራዎችና ግብርናን ከአረንጓዴ አሻራ ጋር በማስተሳሰር የሰራቸው ስራዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል። 

በተለይ የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተሰራው ስራ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ብቻ የስንዴ ምርታማነቷን በ27 በመቶ ማሳደግ መቻሏ ስንዴ ከመሸመት ወደ መላክ የመሸጋገሯ ማረጋገጫ ሆኗል።

በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በዚህ ረገድ የሚታይ ለውጥ እያሳየ ሲሆን በተሰራው ውጤታማ ስራ ባለፈው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከውጭ ስንዴ አላስገባችም። በዚህም 1 ቢሊዮን ዶላር ማዳን መቻሏን የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በቅርቡ ማሳወቃቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 15 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ያመረተች ሲሆን በተያዘው ዓመት ደግሞ ምርቱን ወደ 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።

ይህንኑ ግብ ለማሳካት ደግሞ የስንዴ ማሳዋን በማሳደግ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ለመሸፈን እየሰራች ነው።

ከዚህ ውስጥ በመስኖ የሚለማ ስንዴን በ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በመዝራት በመስኖ የሚለማውን ስንዴ በ54 በመቶ ለማሳደግ እየሰራች ነው።

ይህ ደግሞ በቀጣይ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችል ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናግረዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው የግብርናው ዘርፍ በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የመጀመሪያዎቹ 3 ዓመታት (2013-2015) በዋና ዋና ተግባራት ከዕቅድ በላይ ዕድገት አስመዝግቧል።

በዚህም ዘርፉ  በ2013 ከነበረበት 5 ነጥብ 1 በመቶ በ2014 ወደ 5 ነጥብ 8 በመቶ ያደገ ሲሆን በ2015 ደግሞ 6 ነጥብ 3 በመቶ እድገት አስመዝግቧል።

ግብርናውን ለማሳደግ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የሰብል ምርት ሲሆን ለዘርፉ ማደግ 65 ነጥብ 5 በመቶ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ደን ልማት 8 ነጥብ 6 በመቶ እንዲሁም የእንሰሳት ሃብት ልማቱ 25 ነጥብ 9 በመቶ ድርሻ ይዘዋል።

በ2015 ዓ.ም ጠቅላላ 627 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለማምረት ታቅዶ ከተቀመጠው ግብ በላቀ ደረጃ 639 ሚሊየን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል። 

ከበጋ ስንዴ ልማት ጎን ለጎን  በቅርብ ጊዜ የተጀመሩ የቡና፣ አቮካዶና አኩሪ አተር የመሳሳሉት ትላልቅ የግብርና ልማት ስራዎች በተመሳሳይ  ውጤት ታይቶባቸዋል። 

የአዝርት፣ የአትክልት፣ ፍራፍሬና ስራስር ምርት ከፍተኛ የዕድገት ሽግግር የታየባቸው ናቸው። በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚችል አፈጻጸም መመዝገቡ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን የስንዴ ምርት ከውጭ ገበያ ስትገዛ የኖረች ሲሆን በተለይም በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች አቅርቦቱን ሲያስተጓጉሉት ቆይተዋል።

አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ የስንዴና የገብስ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የቻለች ሲሆን የሩዝ ፍላጎቷን ደግሞ 50 በመቶ መሸፈን ችላለች።

በስንዴ ምርታማነት የተገኘውን ተሞክሮ ወደሌሎች ሰብሎች በማስፋት የገቢ ምርቶችን በቀጣይ ለመተካት በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል።

ይህንን ለማሳካት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል። በተለይ ለግብርና ዘርፉ የተሻለ በጀት መመደቡ፣ እስካሁን ለመጣውና ለወደፊትም ይመጣሉ ተብለው ለሚታሰቡ ለውጦች ትልቅ ምክንያት ነው።

ለምሳሌ የ2015 ዓ.ም. በአገሪቱ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ከተመደበው 786 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ፣ ለግብርናው ዘርፍ 34 በመቶ የሚሆን በጀት ተመድቧል። ይህ ደግም ከለውጡ በፊት ከአሥር በመቶ ያልበለጠ በጀት ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ ያደርገዋል። 

በተጨማሪም መንግሥት ለኩታ ገጠምና ለመስኖ እርሻ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱ፣ ሙሉ በሙሉ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነውን የግብርና ስራ በመስኖ የታገዘ እንዲሆንና አርሶ/አርብቶ አደሩ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያመርት ማድረጉ ውጤቱን ጉልህ አድርጎታል።

እንደ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ቡና፣ አቦካዶ ሁሉ በግብርና ሚኒስቴር ከተያዙና በልዩ ትኩረት ከሚከናወኑ  ዕቅዶች አንዱ የማር ምርትን ማሳደግ ሲሆን፣ በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ እንደተመላከተውም  የማር ምርትን በማዘመን ምርቱን ለማሳደግ በስፋት ይሰራል።

በኢትዮጵያ ለማር ምርት ተስማሚ የሆነ አግሮ ኢኮሎጂና ብዛት ያላቸው ዕፅዋት መኖራቸው የሚመረተው ማር የተፈጥሮ ጥራት እንዲኖረው ያግዛል። ይህንኑ ዕምቅ ሀብት ትኩረት ሰጥቶ ማልማት ከተቻለ ከ500 ሺሕ ቶን በላይ ማርና ከ50 ሺሕ ቶን በላይ ሰም ማምረት እንደሚቻል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ እንስሳት ሀብት ኢንስቲትዩት ባወጣው መረጃ በሀገሪቱ አለ ተብሎ ከሚገመተው ሰባት ሚሊዮን የንብ መንጋ ውስጥ 90 በመቶው በባህላዊ ቀፎ ውስጥ የሚገኝ ነው። የንብ መንጋዎቹ በባህላዊ ቀፎ ከመኖራቸው በተጨማሪ በጫካ መገኘታቸው ሃብቱ ለአገር ዕድገት በሚፈለገው ልክ እንዳይውል አድርጎታል።

ያም ቢሆን ባለፈው ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው “የሌማት ትሩፋት” ለማር ምርት ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ዘመናዊ የንብ ማነብ ዘዴ እንዲስፋፋ ተደርጓል።

በዚህም የማር ምርታማነትን በዓመት ወደ 98 ሺህ ቶን ማሳደግ መቻሉ በቅርቡ መገለጹ ይታወሳል። ምርቱን በእጥፍ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የማር ምርት የማምረት አቅም ካላቸው አሥር ሀገሮች አንዷ በመሆኗ ሃብቱን ለማልማት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል።

በአጠቃላይ መንግሥት ለአረንጓዴ ልማት/አሻራ፣ ለአፈርና አካባቢ  ጥበቃ የሰጠው ትኩረት ሁሉን አቀፍ የግብርና ዕድገት እንዲመጣ መሠረት ሆኗል።

በተጨማሪም መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌማት ትሩፋትና ምግባችን ከደጃችን መርሐ ግብር ኅብረተሰቡ የከተማ ግብርናን እንዲያስፋፉ በገጠርም ሆነ በከተማ ያከናወነው ተግባር ውጤት አስመዝግቧል።

በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ዘርፉን ለማዘመን የተከናወኑ የልማትና የሪፎረም ሥራዎች ግብርናውን ከአዝጋሚ ጉዞ በማውጣት ወደ ፈጣንና አስተማማኝ ጉዞ ማሸጋገር ችለዋል። 

ኢትዮጵያ አሁንም አያሌ ያልተነኩ ዕምቅ ሀብቶች ያሏት መሆኗን እንደ እድል በመውሰድ  ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ ይጠበቅባታል። ይህን ማድረግ ስትችል የግብርና ሽግግር ይረጋገጣል።

ግብርናውን ለማሻገር ደግሞ በፋይናንስ፣ በግብአት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰለጠነ የሰው ሀይል ልማት ላይ በትኩረት መስራት ያሻል። ወጣቱ ግብርናን እንደ ንግድ (Agri-Bussiness) ማየትና በዚያው ልክ መስራት ይጠበቅበታል። 

በዚህ ልክ በርብርብ ሲሰራ ግብርናን በማሸጋገር ገበታን ከመሙላት ወይም ከፍጆታ አልፎ ገበያን ማማተር ይቻላል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም