ለጊፋታ በዓል የምናደርገው ዝግጅት ቁጠባን፣ አብሮነት እና የሥራ ባህልን ለማጠናከር እያገዘን ነው---የወላይታ ዞን ነዋሪዎች 

ወላይታ ሶዶ ፤ መስከረም 13/2016(ኢዜአ)፡-ለ"ጊፋታ" በዓል ዓመቱን ሙሉ የሚደረገው ዝግጅት የቁጠባ ባህላችንን ከማሳደግ ባለፈ አብሮነት እና የሥራ ባህልን ለማጠናከር እያገዘን ነው ሲሉ የወላይታ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

"ጊፋታ" ቂምና ቁርሾን በማስወገድ ተስፋ፣ ልምላሜና የቀጣይ ስኬትን በማለምና በማቀድ የሚቀበሉት የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ነው።

በዓሉ ዓመቱን ሙሉ በሚደረግ ዝግጅት የሚከበር ሲሆን "ጊፋታ" በኩር፣ ታላቅ፣ መሻገር የሚል ትርጓሜም አለው።


 

የብሔሩ ተወላጅ የሆኑ አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ልጆች ባላቸው የሥራ ክፍፍል የእርድ ሰንጋ መግዣ፣ የቅቤና ለሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ዕቁብ በማሰባሰብ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግና የዘመን መለወጫን በዓሉን ለመቀበል ዓመቱን ሙሉ  ይዘጋጃሉ።

በበዓሉም በዓመቱ ጠንክሮ በመስራት ከሌሎች ልቆ የታየ ለሌሎች ተሞክሮ እንዲሆን ይሞገሳል፤ በዘፈንም ይወደሳል። 

በእዚህም ሁሉም በየተሰማራበት  ጠንክሮ በመስራት ውጤታማ እንዲሆን ይበረታታል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የወላይታ ዞን ነዋሪዎች ለ”ጊፋታ” በዓል ዓመቱን ሙሉ የሚደርጉት ዝግጅት የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ነው የገለጹት።

ከነዋሪዎቹ መካከል የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ፈለቀ እንዳሉት "ጊፋታ" ለዓመት በተያዘ ዕቅድ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎበት የሚከበር በዓል ነው።

በወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሬ ታርዶ ቅርጫ እንደተከፋፈለ ለቀጣዩ ዓመት ቁጠባ እንደሚጀመር ገልጸው፣ ለዓመት በሚቆጠበው ገንዘብ ከበዓሉ ባለፈ ለሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች እንደሚውል ተናግረዋል።

ይህም በዓሉ የቁጠባ ባህልን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ሴቶችም ለበዓሉ የሚያስፈልገውን የቂቤ እቁብ በወላይቲኛ "ኦይሳ ሹፋ" በመጣልና እንሰት ፍቆ በማዘጋጀት በዓሉ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳይፈጥር ዝግጅት ያደርጋሉ ያሉት ደግሞ የዞኑ ተወላጅ ወይዘሮ ጸጋ ፈንታ ናቸው።

ይህም ወጪን በመቀነስና የቁጠባ ባህላቸውን ከማሳደግ ባለፈ ህብረትን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

የጊፋታ በዓል ከዘመን መለወጫነት ባለፈ የህዝቡን የቁጠባ ባህል ስለሚያሳድግ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

የሶዶ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ አስደሳች ጆርጌ በበኩላቸው ለጊፋታ ተብሎ የሚጣለው የገንዘብ፣ የቂቤ እና አይብ እቁብ በዓሉን ተረጋግቶ ከማክበር ባለፈ ለልጆቻቸው የትምህርትና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።


 

በሴቶች በኩል የሚደረገው ዝግጅት ቁጠባን እንዲለማመዱና ሕብረትን እንዲያጠናክሩ በማድረግ በዓሉ ኢኮኖሚያዊ ጫና ሳይፈጥር ለማክበር እንደሚረዳም ገልጸዋል።

ይህም ከጥንት ጀምሮ በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ የተለመደ የበዓሉ እሴት በመሆኑ ለሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እየተጠቀሙበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በበኩላቸው የ”ጊፋታ” በዓል ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፓለቲካዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ለበዓሉ ዓመቱን ሙሉ የሚደረገው ዝግጅትም የቁጠባ ባህልን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ተሞክሮውን ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።


 

በዓሉ ህዝቡ የቀደመ የቁጠባ ባህል እንዳለው ከማሳየት በተጨማሪ ዕዳ ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገር የሚያደርግበት እሴት ጭምር ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።

ሰላም፣ አንድነት፣ ይቅርታና ጠንክሮ መስራትን የሚያበረታታው የ”ጊፋታ” በዓል ዕሴቶቹ በአግባቡ ተይዘው ለትውልድ ከማሸጋጋር ባለፈ ለሀገር ልማትና ብልጽግና ሚናውን ለማላቅ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ሳሙኤል እንዳሉት የቁጠባ ባህሉ አቅም የሌላቸውን ከመደገፍ ጀምሮ በህብረተሰቡ ውስጥ አብሮነትን የሚያጠናክር ነው።

የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ የ”ጊፋታ” በዓል የፌዴራልና የክልል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የብሔሩ ተወላጆችና ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመጡ እንግዶች በተገኙበት በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም ዛሬ በድምድቀት ተከብሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም