ለችግሮች ሁሉ በምክክር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የጋራ ሃላፊነታችን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ለችግሮች ሁሉ በምክክር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የጋራ ሃላፊነታችን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 13/2016 (ኢዜአ)፦ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ በምክክር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የጋራ ሃላፊነታችን ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ላይ በማተኮር ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም ለጋራ ሀገራችን የጋራ መፍትሄ የማበጀት ጉዳይ ለማንም የሚተው ሳይሆን የሁላችንንም ጥረትና ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ገዥው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከ60 በላይ የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም ከምንም በላይ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የአገር ሉዓላዊነትንና ህልውናን የሚገዳደር ችግር ሲያጋጥም ጉዳቱ የሀገርና አጠቃላይ የህዝብ በመሆኑ ሁላችንም የመፍትሄው አካል ሆነን መገኘት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሰለጠነ የውይይት ባህልን በማዳበር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ማጠናከርም ይገባል ነው ያሉት።
በመሆኑም የግጭት ምክንያቶችን በመለየትና በንግግር መፍትሄ በመሻት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁላችንም ዝግጁ መሆን አለብን በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በምንም አጋጣሚ የሚፈጠር ችግር መፍትሄ አለው የሚሉት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ፤ በንግግርና በይቅርታ ቅራኔዎችን በመፍታት ብሄራዊ መግባባት መፍጠር አለብን ብለዋል።
በተለያዩ የዓለም አገራት የነበሩ ችግሮች በዘላቂነት የተፈቱት በመነጋገር በመሆኑ በኢትዮጵያም ችግሮች ሁሉ በሃይል ሳይሆን በውይይትና በንግግር ብቻ ሊፈቱ ይገባል ነው ያሉት።
በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።