አገር በቀል ባህሎችና እውቀቶች ለሰላምና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ ጠብቆ ማቆየት ይገባል--የካፈቾ የዘመን መለወጫ በዓል ታዳሚዎች 

ቦንጋ፤ መስከረም13/2016(ኢዜአ)-፡ አገር በቀል ባህሎችና እውቀቶች ለሰላምና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉ በካፈቾ የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የታደሙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። 

የካፈቾ ብሔር የ2016 የዘመን መለወጫ (የመኔ ሸድዬ ባሮን) በዓል በቦንጋ ከተማ በፓናል ውይይት እና በባህል ፌስቲቫል ተከብሯል።

የዘመን መለወጫ በዓሉ ከጥንት የካፋ ንጉስ ጀምሮ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበርና በካፋ ህዝብም ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው በዓል ነው።  

የአካባቢው ተወላጆችና ሌሎች እንግዶች በየዓመቱ መስከረም 12 እና 13 በበዓሉ ለመታደም ወደካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ይመጣሉ።

በዘንድሮ የብሔሩ የዘመን መለወጫ በዓል ላይ ለመታደም ወደቦንጋ ከተማ ከመጡት መካከል ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የመጡት የሺናሻ ብሔረሰብ ተወላጅ ወይዘሮ አስካለ አለቦሮ እንዱ ናቸው።

በዓሉ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር በመሆኑ ለትውልድ ጠብቆ ለማስተላለፍ ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይም ለዘላቂ ሰላም ግንባታና አንድነት መጠናከር ያለውን እሴት አጐልብቶ መጠቀም ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ወይዘሮ አስካለ፣ አብሮነትን ለማጠንከር በበዓሉ መታደማቸውን ገልጸዋል።

በዓሉ ሰላምና አብሮነትን ከማጠንከር ባለፈ በሥራ እና በምክንያታዊነት የሚያምን ትውልድ ከመፍጠር አንጻር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዓሉን ለማክበር ከኦሮሚያ ክልል የመጡትና የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ሻምበል ግርማ ማለቶ ናቸው።


 

በየዓመቱ ወደአካባቢው መጥተው በዓሉን እንደሚያከብሩ ገልጸው፣ በዓሉን በአብሮነት ተሰባስቦ ከማክበር ባለፈ ለአካባቢው ልማትና እድገት በአንድነት መረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል።

እንዲህ አይነት ባህሎች የህብረተሰቡን የእርስ በእርስ ትስስር ስለሚያጠናክሩ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም አቶ ግርማ ተናግረዋል።

የመኔ ሸድዬ ባሮን በዓል ባህላዊ እሴት ሳይጠፋ ለረጅም ዘመናት ከትውልድ ወደትውልድ ሲተላለፍ መምጣቱን የገለጸው የካባቢው ተወላጅ ወጣት ሙሉቀን መንገሻ በበኩሉ፣ በዓሉን ይበልጥ በማልማት ጠብቆ በማቆየት ለዓለም ማስተዋወቅ ይገባል ብሏል።

የካፈቾ የዘመን መለወጫ በዓል ሰላምና አንድነት ከማጎልበት ባለፈ በውስጡ ያሉት ሰርቶ የመለወጥና ሌሎች እሴቶች ለትውልዱ ጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግሯል።


 

"በመሆኑም በአግባቡ በመጠበቅና በማልማት ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋጋር ሁላችንም ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ብሏል። 

እንደ ወጣት ሙሉቀን ገለጻ ወጣቱ ወደውጭ ከማየት ይልቅ የአባቶቹን ባህልና ታሪክ በአግባቡ አውቆ፣ ከመጠበቅ ባለፈ አልምቶ መጠቀምና በማንነቱ መኩራት አለበት።

ሌላኛው የአካባቢው ተወላጅ አቶ አሰፋ ማሙዶ በዓሉ በኃይማኖት፣ በዘር እና በፖለቲካ ልዩነት ሳይኖር በጋራ የሚከበር የአንድነት ተምሳሌት በዓል ነው።


 

የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆና መሠረቱን ሳይለቅ ለትውልድ እንዲሻገር ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።

በዓሉ የህዝቦች አንድነት እንዲጠነክር እና የሥራ ባህል እንዲጎለበት በማድረግ በኩል ያለውን ፋይዳ ለአካባቢውና ለሀገር ልማት ማዋል ይገባል ብለዋል።

ከፓናል ውይይቱ በተጨማሪ በዞኑ ከሚገኙ 12 ወረዳዎችና አምስት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች የተለያዩ ባህላዊ ፌስቲቫሎችን አቅርበዋል።

ኑሯቸውን በተለያዩ አካባቢዎች ያደረጉ የአካባቢው ተወላጆች፣ ከአጎራባች ዞኖች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በበዓሉ ላይ ታድመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም