የጋሞ፣ የጊድቾ እና የዘይሴ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጋሞ፣ የጊድቾ እና የዘይሴ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ እየተከበረ ነው

አርባ ምንጭ መስከረም 13/2016 (ኢዜአ) ፦ የጋሞ፣ የጊድቾና የዘይሴ ብሔረሰቦች "ዮ--ማስቃላ"፣ "ባላ ካዳቤ" እና "ቡዶ ከሶ" የዘመን መለወጫ በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ነው።
የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ "ባህላችን ለዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ባህላዊ ኩነቶችና አውደ ጥናት እየተከበረ ነው።
በዓሉ የዘመን መለወጫ ከመሆኑ በተጨማሪ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የአንድነት መገለጫ በዓል መሆኑንም ገልጸዋል።
በበዓሉ ህዝቡ ዓመቱን ሙሉ ጠብቆ ያቆየውን ፈጣሪውን ከማምስገን ባለፈ የእርቅና የይቅርታ መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ ሞናዬ እንዳሉት በበዓሉ የመስቀል ደመራ ባህላዊ እሴቶች ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።
በተጨማሪም የባህል ተምሳሌትና የህፃናት አጋዥ ማስተማሪያ መጻህፍት እንደሚመረቁ አመልክተዋል።
የባህል ቅርስ እና የግብርና ምርቶችን የሚያስተዋወቅ ኤግዚቢሽን ለበዓሉ ታዳሚዎች ክፍት ሆኗል።
በበዓሉ ላይ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከአጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች የተጋበዙ እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።