የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል በሶዶ ሁለገብ ስታዲየም እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል በሶዶ ሁለገብ ስታዲየም እየተከበረ ነው

ወላይታ ሶዶ ፤መስከረም 13/2016 (ኢዜአ)፡-የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል በሶዶ ሁለ ገብ ስታዲየም በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።
እለቱ በብሔሩ አጠራር "ሹሀ ዎጋ" ወይም የእርድ ቀን በመባል የሚታወቅ ሲሆን አዲሱን ዓመት መቀበያን ምክንያት በማድረግ እርድ የሚፈጸምበት ቀን ነው።
የአዲስ ዘመን መቀበያና የአሮጌው መሸኛ ተደርጎ በሚታየው የጊፋታ በዓል በባህላዊ ጨዋታዎች መከበር የጀመረ ሲሆን ለበዓሉ ድምቀት የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችም ተዘጋጅተዋል።
በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም እየተካሄደ ባለው የበዓሉ አከባበር ላይ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የብሔሩ ተወላጆች የፈረስ ጉግስን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ትእይንቶችን እያቀረቡ ነው።
እንዲሁም የባህሉን እሴቶች የሚገልጹ፣ የተፈጥሮና ባህላዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚያሳዩ፣ የመገልገያ ቁሶችና ሌሎች በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን የሚያሳይ የስዕል አውደ ርዕይ ለበዓሉ ታዳሚዎች ተከፍቷል።
በዓሉን ለመታደም የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ አምባሳደሮች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የህብረተስብ ክፍሎችም በበዓሉ ላይ የተገኙ ሲሆን የፖሊስ ማርሽ ባንድም በጣዕመ ዜማ በዓሉን እያደመቀው ይገኛል።
በበዓሉ ላይ የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ ደመራ የመለኮስ እና ሌሎችም ስነስርዓቶችም እንደሚከናወኑ ይጠበቃል።