ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀጣናው አገራትን የሚያስተሳስር የልማት ፕሮጀክት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀጣናው አገራትን የሚያስተሳስር የልማት ፕሮጀክት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 12/2016 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵዊያንና የቀጣናው አገራትን የሚያስተሳስር የልማት ፕሮጀክት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አቶ ደመቀ ይህንን ያሉት በአሜሪካ ኒው-ዮርክ እየተካሄደ ባለው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ባደረጉት ንግግር ነው።
በንግግራቸውም የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የአገራትን ትስስርን በማሳለጥም የዜጎችን ህይወት በማሻሻል የማይተካ ሚና እንዳለቸው ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የዜጎችን ሕይወት በማሻሻልና የአገራትን ትስስር የሚያጠናከር ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ጎን ለጎንም በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት ለሚካሄድ የሦስትዮሽ ድርድም ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና አለመረጋጋት ችግሮችን ለመፍታት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትብብር ይጠይቃል ብለዋል።
ሱዳንም ከገባችበትን ውስጣዊ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንደምትፈታ ያላቸውን እምነት ጠቁመው ኢትዮጵያም ለሱዳን ሰላምና ደኅንነት የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።
የሰላም ሂዳትን ለማጠናከር በትብብር መሥራት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደመቀ፤ ኢትዮጵያም ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።
በዚህ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ገንቢ ሚናዋን በመወጣት በኢኮኖሚያዊ ትብብር ለተመሰረተ የልማት እንቅስቃሴ መሳለጥ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ አንስተዋል።
ከጉረቤት አገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት በማሳደግ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቀጣናዊ የመሰረተ ልማት ውህደት እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝም አብራርተዋል።
የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን ለመቅረፍም በትብብር ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ አካሄድን መከተል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።