የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 12/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ። 

አቶ ደመቀ መኮንን ይህንን ያሉት በአሜሪካ ኒው-ዮርክ እየተካሄደ ባለው በ78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

በንግግራቸውም የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸው ተጽዕኖው በአፍሪካና በሌሎች በማደግ ላይ ባሉ አገራት ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ያደጉ አገራት አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የአየር ንብረትን ለውጥን እንዲቋቋሙ ለመልቀቅ የወሰኑትን የገንዘብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ አለመለቀቁን አንስተዋል።

እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ቀውስ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ እንዲሰጥ እየሰራች መሆኑን ገልጸው አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የዚህ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል።

መርኃ ግብሩ የአረንጓዴ ልማትን ለማስፋት ዓላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ መርኃ ግብሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ልምድ ለማካፈል እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል። 

በቀጣይ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ችግሩን ለማቃለል ተጨባጭ እርምጃ ለመውሰድ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

በሌላ በኩል አንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 ድኅነት ለመቀነስ እየተሰራ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህ ችግሮች እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል። 

ጎን ለጎንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለው የሸቀጦች የዋጋ ንረት የአብዛኛውን ተጋላጭ ማኅበረሰቦች ፈተና ይበልጥ እያወሳሰበው መሆኑንና ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመዋል። 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም