መምሪያው ህዝቡን ደጀን አድርጎ ሰላም የማስጠበቁን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል

ድሬዳዋ፤  መስከረም 12 ቀን 2016(ኢዜአ)፡- የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ህዝቡን ደጀን በማድረግ  የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቁ ስራ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቅላይ መምሪያው ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ ገለጹ። 

የተቀየረውን የአስተዳደሩ የመደበኛ ፖሊስ የደንብ ልብስ  የማልበስ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል።

ኮሚሽነር ዓለሙ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ፤ ፖሊስ ህዝብን ደጀን አድርጎ የድሬዳዋና የአካባቢዋን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ ደረጃ እየጠበቀ ነው።

በድሬዳዋ በተከናወኑ የተቀናጁ ስራዎች ከለውጥ በፊት ሲከሰቱ የነበሩት የፀጥታ ችገሮች ተወግደው በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።


 

እንደ ኮሚሽነር ዓለሙ ገለጻ ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን መመሪያ ተከትሎ የድሬዳዋ አስተዳደር የመደበኛ ፖሊስ የደንብ ልብስ እንዲለወጥ ተደርጓል።

በፌደራል ፖሊስ የወጣውን ወጥ አደረጃጀትና የደንብ ልብስ  መመሪያ ተከትሎ የፖሊስ ኃይሉን በተለያዩ ዘርፎች በማጠናከር የተጀመረውን የሰላምና የፀጥታ የማስከበር ስራ ያጠናክራል ብለዋል።

የተለወጠው የመደበኛ ፖሊስ የደንብ ልብስ ዛሬ በተካሄደው የማልበስ ሥነ-ሥርዓት ላይ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አመራሮችና አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም