የዓለም የጸጥታ ዘርፍ ቅኝት የሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበረ፣ ባለብዙ ወገን ትብብር እና አካታችነትን የተከተለ ሊሆን ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም የጸጥታ ዘርፍ ቅኝት የሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበረ፣ ባለብዙ ወገን ትብብር እና አካታችነትን የተከተለ ሊሆን ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 12/2016(ኢዜአ)፦ የዓለም የጸጥታ ዘርፍ ቅኝት የሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበረ፣ የባለብዙ ወገን ትብብር እና አካታችነትን የተከተለ እንዲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።
አቶ ደመቀ ይህን ያሉት "ሰላም፣ ብልፅግና፣ ለውጥና ዘላቂነት" በሚል መሪ ሀሳብ በአሜሪካ ኒዮርክ እየተካሄደ ባለው 78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ኢትየጵያ ለመንግስታቱ ድርጅት መመስረት ታሪካዊ ሚና እንደተጫወተች ሀገር የጋርዮሽ ዓለም እንዲኖር ትሻለች ብለዋል።
የነበረው አካታች ያለሆነ መዋቅር የጋራ ፍላጎትን ለማስፈጸም የማያስችል በመሆኑ ሁላችንም በተባበረ መንገድ የባለብዙ ወገን ስርዓት ለመዘርጋት አቋም ሊኖረን ይገባል ብለዋል።
አለም አቀፋዊ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን ከተፈለገ አዲሱ የዓለም የጸጥታ ስርዓት የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበረ መሆን እንዳለበት ኢትዮጵያ በጽኑ እንደምታምን ነው አቋሟን የገለጹት።
ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ሰላም ማስከር ተልዕኮ ስር ለዓለም ሰላም ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ሀገር የጸጥታው ምክር ቤት ሪፎርም የምርጫ ሳይሆን ፍጹም አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ እንደምታምን ተናግረዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት አሳታፊ አና አካታች ሆኖ መዋቀር ያሻዋል ያሉት ምከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በምክር ቤቱ ለአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ የመስጠት ጉዳይ ፖለቲካዊ፣ ሞራላዊና ፍትሃዊ ውሳኔ የመስጠት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ለአፍሪካ የሰላም ተልዕኮ በቂ የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት እና ለሀጋራት የህግ ማስከበር ስራዎች ስኬታማነት አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተናጠላዊ ማዕቀብ እና ተገቢ ያልሆኑ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች የመንግስታቱን ድርጅት መርህና አሰራር የሚጣረሱ በመሆኑ ኢትዮጵያ በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚጣሉ መሰል እርምጃዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊነሱ ይገባል ብላ እንደምታምን አንስተዋል።
በሉዓላዊ ሀገራት መካከል የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በተናጠላዊ ማዕቀብ ሳይሆን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት መፍታት አማራጭ መሆን እንደላበትም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያና መሰል ታዳጊ ሀገራት የመንግስታቱ ድርጅት አጠቃላይ ቅርጽ መስተካከል እንዳለበት ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
አሁንም ይበልጥ አካታች፣ ውጤታማና ለብዝሀነት የተመቸ እንዲሁም ታዳጊ ሀገራትን ታሳቢ ያደረገ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የተቀላቀለችበት 'ብሪክስ' በዚህ ረገድ ትልቅ ምሳሌ መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለልማት ግቦች ስኬት የፋይናንስ አቅርቦት ቢኖርም በታዳጊ አገራት ግን ፍትሃዊነት የጎደለው በመሆኑ ይህንን ለማስተካከል አዲስ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር ይፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊና የበለጸገ ማህበረሰብ ለመገንባት የልማት ግቦችን ቀርጻ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው፤ ለዚህ ግን አዲስ የሆነ አካታች ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርዓት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላምና ዴሞክራሲ መስፈን ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ችግር የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የመፍታት መርህ በፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መፍታት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
ስምምነቱ በመልካም አፈጻጸም ላይ መሆኑን ጠቀስው፣ ከሰላም ስምምነቱ ባሸገርም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ የሽግግር ፍትህ ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ለኢትዮጵያዊያን የተሻለ እና ብሩህ ነገ ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።