አገራዊ ምክክሩን በስኬት ለማካሄድ ሕዝቡ ተሳትፎውን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩን በስኬት ለማካሄድ ሕዝቡ ተሳትፎውን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 12/2016(ኢዜአ)፦አገራዊ ምክክሩን በስኬት ለማካሄድ ሕዝቡ ተሳትፎውን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ለውይይት የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የሚለዩና በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮችን ምርጫ ከመስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ወረዳዎች እያከናወነ ነው።
በዛሬው ዕለትም በጉለሌና ልደታ ክፍለ ከተማ በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮች ምርጫ ተከናውኗል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተካሄደው መርኃ-ግብር የተገኙት ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ፤ ሁሉን ያሳተፈ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመምረጥ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ይህም በአገር ደረጃ የማያግባቡ ልዩነቶችን ከመሠረቱ በመለየት በሕዝብና መንግሥት እንዲሁም በሕዝቦች መካከል መተማመን ለመፍጠርና ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ሕብረተሰቡም ተወካዮችን ለመምረጥ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ከመምረጥ ጎን ለጎንም ለሚመርጡ ተወካዮች መነሻ የአጀንዳ ሃሳብ በመስጠት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በልደታ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ለአጀንዳ ልየታ ተወካዮች ምርጫ የተገኙት ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቅ ጌቱ በበኩላቸው፤ ሕብረተሰቡ በአገራዊ ምክክሩ አጠቃላይ ሂደት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
በልደታ ክፍለ ከተማ በተካሄደው መርኃ-ግብር የተገኙት ወይዘሮ ፋናዬ መንግሥቱ፤ አገሪቱን ከተለያዩ ተግዳሮቶች ለማውጣት ሁሉም ማኅበረሰብ የኮሚሽኑን ጥረት መደገፍ አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠላም የሁሉም ሠላም መሆኑን ገልጸው፤ መድረኩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ መሆኑን የተገነዘብንበት ነው ብለዋል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተካሄደው መርኃ-ግብር የተሳተፉት አቶ ወንድወሰን አጎናፍር በበኩላቸው፤ በሁሉም የምርጫ መዋቅር አካታች ምርጫ መካሄዱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።