የአገር መከላከያ ሠራዊት በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ያተረፈውን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምና ዝና አስጠብቆ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 12/2016(ኢዜአ)፦ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ያተረፈውን ውጤታማ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምና ዝና አስጠብቆ እንደሚቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ ገለጹ።

ዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በግጭት አፈታትና ሠላም ማስከበር ሙያ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች አስመርቋል።

በዚሁ ወቅት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የሠላም ማስከበር ግዳጅ ከበሬታ የተጎናጸፈች አገር ናት ብለዋል።

በቀጣይም የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በብቃት በመወጣት ሠራዊቱ በሚሰማራበት ቦታ ሁሉ በመስዋዕትነቱ ያተረፈውን የከበረ ስምና ዝና ተጠብቆ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ተመራቂ ከፍተኛ መኮንኖቹም ቀጣይ የሚሰጣቸውን ወታደራዊ ግዳጅ በብቃት በመወጣት የአገራቸውን ታሪካዊ የሠላም ማስከበር ውጤታማ የግዳጅ አፈጻጸም ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የሠላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ፤ መከላከያ ባካሄደው የለውጥ እርምጃ የሠራዊቱን አቅም ማጎልበት የሚያስችል ትምህርትና ሥልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ በግጭት አፈታትና ሠላም ማስከበር ሙያ ብቁ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን በማሰልጠን ዛሬ ለምርቃት ማብቃታቸውን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ፤ ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር በሁለንተናዊ ዘርፎች የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ዘርፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ አገር መሆኗን ጠቁመው፤ ኢንስቲትዩቱ የሚያስመርቃቸው ሙያተኞችም በሠላም ማስከበር የአመራር ቦታዋን ለማስጠበቅ ጉልህ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዛዥ ኮሎኔል ደመቀ መንግሥቱ፤ ተቋሙ በግጭት አፈታትና ሠላም ማስከበር ሙያ ብቃት ያላቸው የጦር መኮንኖችን እያፈራ ነው ብለዋል።

ተመራቂዎቹም የሚፈለገውን መስፈርት በማሟላት ሦስት ከጎረቤት አገራት የመጡ መኮንኖችን ጨምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 20 ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን በሁለተኛ ዲግሪ ማስመረቁን አስታውቀዋል።

ተመራቂ ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹም ለሁለት ዓመታት ሲከታተሉት የቆዩት ትምህርትና ሥልጠና የቀጣይ ግዳጃቸውን በእውቀትና በብቃት መወጣት የሚያስችል ግንዛቤ መያዛቸውን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በግጭት አፈታትና ሠላም ማስከበር በሁለተኛ ዲግሪ ሥልጠናውን የሰጠው ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ባደረገው የቴክኒክ ድጋፍና የጃፓን መንግሥት ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ እንደሆነ ተገልጿል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ተወካዮችና ወታደራዊ አታሼዎች ጨምሮ የተመራቂ ቤተሰቦችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም