ኩባንያው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የምታስገባውን የታጠበ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ስራ ጀምሯል- ዮ ሆልዲንግ ንግድ እና ማኑፋክቸሪንግ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 12/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የምታስገባውን የታጠበ የድንጋይ ከሰል  በሀገር ውስጥ የሚተካ ፋብሪካ አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ዮ ሆልዲንግ ንግድ እና ማኑፋክቸሪንግ የተሰኘው ሀገር በቀል ኩባንያ አስታወቀ።

'ዮ ሆልዲንግ ንግድ እና ማኑፋክቸሪንግ' የተሰኘው ሀገር በቀል ኩባንያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የድንጋይ ከሰል እጥበት ፋብሪካ ገንብቶ ወደ ምርት መግባቱን የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል።

ኩባንያው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታወጣበትን የድንጋይ ከሰል ምርት የማቀነባበር ሥራውን ይበልጥ ለማሳደግ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ውል ለማሰር በሂደት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኩባንያው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አታክልቲ ተስፋዬ እንዳሉት፤ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 በግማሽ ቢሊየን ብር ካፒታል ያቋቋመው ዮ ሆልዲንግ ሥራ ጀምሯል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገነባው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሲጠይቅ የኖረውን የታጠበ የድንጋይ ከሰል ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር ውስጥ ማቀነባበር ጀምሯል ብለዋል።

የድንጋይ ከሰል ማምረትና ማቀነባበር ሂደቱን ለማሳለጥ እና የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ለማምጣት የካበተ ልምድ ካላቸው የውጭ ኩባንያዎች ጋር ለመሥራት የሚያስችል ውል ለማሰር ዝግጅት አጠናቋል ብለዋል።

ፋብሪካው አሁን ላይ የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የወረቀት፣ የሴራሚክ፣ የጂፕሰም እና ሌሎች ፋብሪካዎች ግብዓትነት የሚውል በዓመት 1 ሚሊየን ቶን የታጠበ የድንጋይ  ማቅረብ እንደሚችል ጠቅሰዋል።

እስካሁን ለ200 ኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልፀው፤ ግብዓቱን ለተለያዩ ፋብሪካዎች በቀላሉ ማቅረብ የሚችል ነው ብለዋል። 

የኩባንያው የግብይትና ቢዝነስ ልማት ኦፊሰር ይታሰብ ደጉ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው ወደ ሙሉ የማምረት አቅም ሲገባ 2 ነጥብ 16 ሚሊየን ቶን በዓመት የታጠበ የድንጋይ ከሰል እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል።

ፋብሪካው አገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ጫና የማቃለል እና በሂደትም ወደ ውጭ በመላክ ገቢ የማምጣት ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል።

የኩባንያው የአቅርቦት ሰንሰለት ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ፍቅሬ በበኩላቸው፤ በዮ ሆልዲንግ ብቻ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር  በ2020 በተጠቀሰ መረጃ ከውጭ የምታስገባውን የታጠበ የድንጋይ ከሰል  95 በመቶ ለመሸፈን ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል። 

በዮ ሆልዲንግ ተሳትፎ ብቻ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ እስከ 5ኛ ደረጃ ከሰል አቅራቢ ሀገር እንድትሆን እንደሚያደርግም ነው የሥራ ኃላፊዎቹ የጠቀሱት።

የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ኤፍሬም ታደሰ በበኩላችው፤ ፋብሪካው በክልሉ 7ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ድንጋይ ከሰል ለማውጣት ፈቃድ ወስዷል።

ድርጅቱ ባደረገው ጥናት በሥፍራው ከ40 እስከ 50 ዓመት የሚያቆይ የድንጋይ ከሰል ክምችት እንዳለው ተናግረዋል።

በዮ ሆልዲንግ የማዕድን ዘርፍ አስተባባሪ ኤርሚያስ ወልዴ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው በአካባቢው ብክለት ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንዳያሳድር የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት መሆኑን ገልፀዋል።

የከሰል ማውጫ ሥፍራዎችና አካባቢውን መልሶ በማልማት የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንደሚያከናውን ጠቁመዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም