በአማራ ክልል 250ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው- የክልሉ ግብርና ቢሮ

ባህርዳር መስከረም 12/2016 (ኢዜአ)... በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወቅት 250ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የዞን አመራሮችና ባለሙያዎችን ያሳተፈ ወቅታዊ የግብርና ስራዎችን የገመገመና የቀጣይ አቅጣጫዎች ያስቀመጠ የውይይት መድረክ ዛሬ በባህርዳር አካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በክልሉ በዘንድሮው የበጋ ወቅት 250 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ በማልማት 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

በመስኖ ስንዴ ልማቱ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችን በመደገፍና በማበረታት በክልሉ ያለውን የከርሰና የገፀ ምድር የውሃ ሃብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ዕቅዱን ለማሳካት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።

በተለይ በዚህ ዓመት አዲስ ወደ ልማት የሚገቡና ቀደም ሲል የገቡ ዘመናዊ የመስኖ ግድቦችንና የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በመጠቀም ዕቅዱን ለማሳካት በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የበጋ ስንዴ መስኖ ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን ከግማሽ ሚሊዮን  ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና ከ200 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ እንደሚውልም ተናግረዋል። 

አርሶ አደሩም የዘር እጥረት እንዳይገጥመው ባለፈው ዓመት ካመረተው ዘር እርስ በርስ በመለዋወጥ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን እንዲያከናውን ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ በየደረጃው ያለው አመራር፣ የግብርና ባለሙያና አርሶ አደሩ የተቀናጀ ርብርብ እንዲያደርግ አቶ አጀበ አሳስበዋል። 

የዝናብ ስርጭት መቆራረጥን ጨምሮ በሌሎች ምክንያቶች በመኽር ልማቱ ለያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ በመስኖ ልማቱ ለማካካስ በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል። 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ ቀኝአዝማች መስፍን እንዳሉት በዞኑ በዘንድሮው የበጋ ወቅት 26 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 1 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ታቅዷል።


 

አያይዘውም የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረትን እንዳያጋጥም ከሚመለከተው አካል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ በቀለ ወርቁ በበኩላቸው ዞኑ አዲስ የተቋቋመ ቢሆንም ራሱን በሰው ሃይልና በስራ መሳሪያዎች አደራጅቶ ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዞኑ ለመስኖ ልማት አመቺ በመሆኑ አርሶ አደሩ ያለውን የውሃ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል

በክልሉ በቀዳሚው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው 213 ሺህ ሄክታር መሬት 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም