በቡናው ዘርፍ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት የተሻለ ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ርብርብ ይደረጋል- ባለሥልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በቡናው ዘርፍ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት የተሻለ ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ርብርብ ይደረጋል- ባለሥልጣኑ

ቦንጋ፤ መስከረም 12/ 2015 (ኢዜአ)..በያዝነው በጀት ዓመት በቡናዉ ዘርፍ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት የተሻለ ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አሳሰበ።
"የቡና ምርት ጥራት ለጋራ ብልጽግናችን" በሚል መርህ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል።
በዚህ ወቅት የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር እንዳሉት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ አረዳድ ይዘው ከምርት ጥራትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለማቅረብ ሊረባረቡ ይገባል።
በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበው የቡና ምርት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው በተያዘው በጀት ዓመት 350 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን አስታውቀዋል።
ዓምና ለውጭ ገበያ ከቀረበው የቡና ምርት ውስጥ የኦሮሚያና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመዋል።
ከነዚህ ክልሎች በ2016 የምርት ዘመን የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለትና ደረጃ ሶስት ምርት በብዛት ማቅረብ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
ከብድር፣ ከሰርተፊኬሽን ማዕከል ፣ ከኬሻና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸውው አካላት ጋር በመቀናጀት እልባት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ተወካይ አቶ ዮሐንስ መላኩ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ክልሉን በሰፊው እየደገፈ መሆኑን በጠንካራነት አንስተዋል።
በቀጣይም ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት በቡናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ቡናን በብዛትና በጥራት ለማቅረብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በቡና ግብይት ዙሪያ ከዘርፉ ተዋናዮች የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቅሰው በክልሉ የሚገኙ አምራቾችን፣ አቅራቢ ባለሀብቶችን እና አርሶ አደሮችን አቅም በመገንባት በጥራት ዙሪያ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።
የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኩጁአብ በቡና ዘርፍ አርሶ አደሩ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።
በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት 64 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ተቅዶ 42 ሺህ ቶን መቅረቡን ጠቁመው የምርት መጠን መቀነስ፣ የአለም የቡና ዋጋ መውረድ እና ህገወጥ የቡና ዝውውር መበራከትና ሌሎች ጉዳዮችን ለዕቅዱ አለመሳካት በምክንያትነት አንስተዋል።
ይህንን ዝቅተኛ አፈጻጸም በያዝነው በጀት ዓመት በማሻሻል 69 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በጥራት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ የቡና ግበይትን ለመከላከል በተደረገ ቁጥጥር 138 ሺህ ቶን ቡና መያዙን ገልጸው 128 ሺህ ቶኑን በህጋዊ መንገድ በመሸጥ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።
ከመድርኩ ተሳታፊዎች መካከል የቡና አልሚና ላኪ አቶ ዝናቡ አባመጫ እንዳሉት ለቡና ጥራት መጓደል ሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች ድርሻ አላቸው ብለዋል።
ቡናን በጥራት እያመረቱ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ገልፀው በአካባቢያቸው ከሚገኙ 260 አርሶ አደሮች ጋር ትስስር በመፍጠር የስልጠና፣ የግብዓት እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።