ወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች የድርሻውን እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች የድርሻውን እያበረከተ ነው
ደሴ ፤ መስከረም 12/2016 (ኢዜአ)፡- ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠነ የሰው ኃይል በጥራትና በብቃት በማፍራት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ስኬት የድርሻውን እያበረከተ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አወል ሰይድ ገለጹ፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 313 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ፡፡
ዶክተር አወል ሰይድ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠነ የሰው ኃይል በጥራትና በብቃት በማፍራት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ስኬት የድርሻውን እያበረከተ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በደሴና ኮምቦልቻ ካምፓሶች አስተምሮ ካስመረቃቸው መካከል 462ቱ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያስተማራቸው ሲሆኑ 578ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።፡
ዩኒቨርሲቲው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ በሶተኛ ድግሪ መርሃግብር ሁለት ተማሪዎችን ማስመረቁንም አስረድተዋል።
የዕለቱ ምሩቃን በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው ለስኬት የበቁ የፅናት ተምሳሌት መሆናቸውን ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና ካስፈተናቸው ተማሪዎች መካከል 74 በመቶ አልፈዋል ብለዋል፡፡
ዶክተር አወል ተመራቂዎች በሙያቸው ህዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል እየተካሄደ ባለው ሀገረ መንግሥት ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ አካዳሚ ተወካይና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ቴዎድሮስ ፈረደ የዕለቱ ተመራቂዎች ኮቪድና ጦርነት ሳይበግራቸው በፅናት ለምረቃ መብቃታቸውን አድንቀዋል።
ስራ ጠባቂ ሳይሆኑ በየሙያቸው የራሳቸውን ስራ ፈጥረው በሀገር ኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተዋናይ በመሆን አገራቸውንና ህዝባቸው ተጠቃሚ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ ሰላምም የድርሻቸውን ለመወጣት ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የቀሰመችውን እውቀት ሀገሯንና ህዝቧን በታማኝነት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸችው ደግሞ በሶሻል ወርክ የተመረቀቸው ሶፍያ ኢብራሂም ናት፡፡
"በርካታ ችግሮችን አልፌ ለዛሬ ምርቃን በመድረሴ ተደስቻለሁ" ያለችው ሶፊያ ለቤተሰቦቿና ለመምህሮቿ ምስጋና አቅርባለች፡፡
የማርኬቲንግ ተመራቂው አማኑኤል ፈጠነ በበኩሉ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናው አልፈን ለዛሬ ምርቃት መድረሳችን ደስታችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል ብሏል፡፡
የመንግሥት ስራ ብቻ ሳይጠብቅ የራሱን አማራጭ ጭምር ተጠቅሞ ህዝብና ሀገርን ለማገልግል ዝግጁ መሆኑንም ተናግሯል፡፡
በምርቃው ሥነሥርዓት ላይ ተመራቂ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።