የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሦስትዮሽ ሁለተኛ ዙር ውይይት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሦስትዮሽ ሁለተኛ ዙር ውይይት ተጀመረ
አዲስ አበባ፤መስከረም 12/2016 (ኢዜአ)፦ሁለተኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦች እና መመሪያዎች ላይ የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ወገን ተደራዳሪዎች ልኡካን መሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ይህ ውይይት እየተካሄደ ያለው እ.ኤ.አ. በ2015 በተደረሰው የመርሆዎች መግለጫ መሰረት በስኬት ከተከናወነው አራተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በኋላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በዚህ ዙር ውይይት አገራቱ በጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ ለመድረስ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አያይዘውም በመርሆዎች መግለጫው በተቀመጠው መሰረት በአባይ ውሃ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ማስፈን ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሒደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በቁርጠኝነት የበኩሏን ሚና እንደምትጫወትም አረጋግጠዋል።
የግብጽ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ሐኒ ሴዊላም(ፕ/ር) እና የሱዳን ተጠባባቂ የውሃ ሚኒስትር ዳውልበይት አብድልረህማን ማንሱር ባሽር በመክፈቻ ንግግሮቻቸው በድርድሩ ሒደት ከስምምነት ላይ ለመድረስ ያላቸውን ፅኑ ተስፋ መግለጻቸውን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።