ታሪኩን የሚያውቅና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ልጆች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ መጽሐፍ ማዘጋጀት ያስፈልጋል- ደራሲ የዝና ወርቁ - ኢዜአ አማርኛ
ታሪኩን የሚያውቅና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ልጆች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ መጽሐፍ ማዘጋጀት ያስፈልጋል- ደራሲ የዝና ወርቁ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2016 (ኢዜአ)፦ ታሪኩንና ባህሉን የሚያውቅና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ልጆች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ መጽሐፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኀበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ደራሲ የዝና ወርቁ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ባሏት የቱሪስት እና ባህላዊ መስህቦች ላይ ያተኮረ "ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የህፃናት መጽሐፍ በዛሬው ዕለት በብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኀበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ደራሲ የዝና ወርቁ እንዳሉት ታሪኩን የሚያውቅና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ልጆች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ የህፃናት መጽሐፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው ።
በተጨማሪ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ሀገራቸውንና ወገናቸውን የሚወዱ ዜጎችን ለማፍራት መጻሕፍት መተኪያ የሌለው ዐቢይ መሳሪያ መሆኑን ተናግራለች።
የህፃናት መጻሕፍትን ለማዘጋጀት ከቋንቋ አጠቃቀም ጀምሮ ልዩ ጥንቃቄና ዕውቀትን በሚጠይቅበት ሁኔታ በሥዕላዊ መረጃ አስደግፎ ደራሲው መጽሐፉን ማቅረቡንም አመስግናለች።
የመጽሐፉ ፀሐፊ መምህርና የሕግ ባለሙያ ሞገስ ጌትነት መጽሐፉ ልጆች አካባቢያቸውንና የሀገራቸውን ባህል እንዲያውቁ በማሰብ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።
ብዙ ጊዜ የህፃናት መጻሕፍት ሲፃፉ ተረቶች ላይ ያዘነበሉ በመሆናቸው ታሪካቸውንና ባህላቸውን የሚያስገነዝቡ መጻሕፍትም አስፈላጊ በመሆናቸው መጽሐፉ ተጽፏል ብሏል።
ይህም ልጆች የበለጠ የንባብ ባህላቸውን እንዲያበለጽጉ እንደሚያግዝ ነው የገለፀው።
ወላጆችም ልጆቻቸውን ከቀለም ትምህርት ባለፈ ሁለንተናዊ ዕውቀት እንዲያዳብሩ መጻሕፍትን ለልጆቻቸው ማስነበብ እንዳለባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል።
ወላጆችም ልጆቻቸውን ከቀለም ትምህርት ባለፈ ሁለንተናዊ ዕውቀት እንዲያዳብሩ እንደዚህ ዓይነት መጻሕፍትን በመግዛት ለልጆቻቸው ማስነበብ እንዳለባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል።