የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2016 (ኢዜአ)፦ የሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ቁልፍ ሚና እንዳለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
78ተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ "ሰላም ፣ብልፅግና ፣ለውጥና ዘላቂነት" በሚል መሪ ሀሳብ በኒው ዮርክ መካሄዱን ቀጥሏል።
በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ከጉባኤው በተጓዳኝ "ለፋይናንስ አካታችነት ትግበራ የሴቶች ምልከታ አስፈላጊነት እና የኢትዮጵያ ተሞክሮዎች" በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ሁነት ዛሬ ተካሄዷል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣የተመድ አባል አገራትና የተመድ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ሴቶች በሁሉም የሕይወት መስኮች ተሳታፊነታቸውን ማረጋገጥ የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባትና ዓለም አቀፍ ግብ የሆነውን የ2030 ዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት ቁልፍ መሆኑን አቶ ገልጸዋል።
ፍትሐዊ የሴቶች ውክልና ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ወሳኝ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የፋይናንስ አካታችነት በመተግበር ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሴቶች ድርጅት(UN Women) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሞኤዝ ዶሬድ ኢትዮጵያ በፋይናንስ አካታችነትና የዘላቂ ልማት ግቦች ያላትን ተነሳሽነት አድንቀዋል።
የዲጂታል ትስስርን ማረጋገጥ ለፋይናንስ አካታችነት ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።