ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና አልጄሪያ መካከል ቀጥታ በረራ መጀመሩ የሁለቱን  ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያግዛል - አምባሳደር ነብያት ጌታቸው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና አልጄሪያ መካከል ቀጥታ በረራ መጀመሩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር  ነብያት ጌታቸው  ገለጹ።

የአልጄሪያ  አየር መንገድ "ኤር አልጀሪ" ከአልጀርስ ወደ አዲስ አበባ ቀጥታ በረራ ዛሬ ጀምሯል፡፡

በመጀመሪያ በረራውም በአልጄሪያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ዮሴፍ ቻሮፍ የተመራ ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

የልዑክ ቡድኑ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል፡፡

በኢትዮጵያና አልጄሪያ መካከል የቀጥታ በረራ እንዲኖር ለማስቻል ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶች አሁናዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ታድሰው ተግባራዊ እንዲደረጉ በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየቱም ተገልጿል፡፡

ከዚህ አኳያ በቅርቡ የሁለቱ አገራትን የትራንስፖርትና አቪዬሽን ዘርፍ ትስስር ለማጠናከር መግባባት ላይ መደረሱ ይታወሳል፡፡

በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር  ነብያት ጌታቸው በዚሁ ወቅት፣ ኢትዮጵያና አልጄሪያ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሆኖም ሁለቱ ሀገራት የቀጥታ የአየር ትራንስፖርት ትስስር እንዳልነበራቸው አስታውሰው፤ በቅርቡ በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል በተደረሰ መግባባት የቀጥታ በረራው መጀመሩን ገልጸዋል።

ይህም ሁለቱ ሀገራት ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የአልጄሪያ የትራንስፖርት ሚኒስትር  ዮሴፍ ቻሮፍ በበኩላቸው፣የቀጥታ በረራው የሁለቱ አገራት ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነት  በንግድና ኢንቨስትመንት በማጠናከር ወደ ላቀ የጋራ የትብብር መስክ  እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል፡፡

የኤር አልጄሪ ዋና ስራ አስፈጻሚ ያሲኔ ቤንስሊማን፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የቀጥታ የአየር ትራስፖርት በረራ መጀመሩን አስመልክቶ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የቀጥታ በረራው ዘወትር ሰኞና አርብ ከአልጀርስ ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ዘወትር ማክሰኞና ቅዳሜ ከአዲስ አበባ ወደ አልጀርስ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቷ ከ63 በላይ ከተሞች በመብረር አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር ያስተሳሰረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤር አልጄሪ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው በቀጣይም ይህንኑ በሚያጠናክሩበት ሁኔታዎች ላይ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

 ዛሬ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ የገባው የአልጀሪያ የልኡክ ቡድን ኢትዮጵያ እየተገበረች ላለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድጋፉን ለማሳየት የወይራ ችግኞችን ይዞ መምጣቱ ተገልጿል፡፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በነሃሴ 2014 ዓ.ም በአልጀሪያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት አብዱልመጅድ ታቡኔ ጋር የሁለቱን አገራት ትስስር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም