በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን ወዳጅነት በፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ይገባል- የፓኪስታን ሴኔት ሊቀመንበር መሐመድ ሳዲቅ ሳንጅራኒ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን ወዳጅነት በፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ይገባል- የፓኪስታን ሴኔት ሊቀመንበር መሐመድ ሳዲቅ ሳንጅራኒ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን ወዳጅነት በፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የፓኪስታን ሴኔት ሊቀመንበር መሐመድ ሳዲቅ ሳንጅራኒ ተናግረዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን ሴኔት ሊቀመንበር መሐመድ ሳዲቅ ሳንጅራኒ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን ትብብር ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
አምባሳደር ጀማል በከር በዚህ ወቅት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ጠቅሰው፤ የፓኪስታን ባለሃብቶች ይህን እድል እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሴኔቱ ሊቀመንበር መሐመድ ሳዲቅ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ጠንካራ ትስስር በጋራ ተጠቃሚነትና መደጋገፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህም ከሁለትዮሸ ባለፈ በባለብዙ ወገን መድረኮች ጠቀሜታ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን ካራቺ በረራ መጀመሩ ሁለቱ አገራትን ብቻ ሳይሆን ፓኪስታንን ከመላ አፍሪካ ጋር የሚያስተሳስር መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነትን በማጠናከር የአገራቱን ወዳጅነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ይህ ትብብር እንዲጠናከር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ማረጋገጣቸውን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።