የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር መንግስት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
ማህበሩ 16ኛውን ዓመታዊ ጉባዔ የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች እና እህት ማህበራት በተገኙበት እያካሔደ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር በዋናነት የሰመመን ሰጪ ህክምና ባለሙያዎችን በመያዝ የተደራጀ ማህበር ነው፡፡
ማህበሩ በኢትዮጵያ የዘርፉ የባለሙያዎችን ቁጥር ከጥራት ጋር ለማሳደግ ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ነው የሚገልጸው፡፡
የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሲራጅ አህመድ ማህበሩ የህክምና አገልግሎቱን ከሌሎች ተያያዥ የህክምና ዘርፎች ጋር በማስተሳሰር ባለሙያዎች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የተለያዩ ስልጠናዎችን በአካልና በኦን ላይን ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ይህን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በመድረኩ ጤና ሚኒስቴርን ወክለው ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴሩ የሰው ሃብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰግድ ሳሙዔል በበኩላቸው፣ ማህበሩ ለኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ብቁ ባለሙያ ማፍራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ማህበሩ በስርዓተ ትምህርት ቀረጻና ክለሳ ዙሪያ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ማህበሩ መንግስት ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በመድረኩም የማህበሩን ያለፈው አንድ ዓመት የስራ አፈጻጸም በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡ ይሆናል፡፡