ሉሲዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሉሲዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ)፦ በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከብሩንዲ አንድ አቻ ተለያይቷል።
በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዋ ረድኤት አስረሳኸኝ በ39ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው ግብ ቡድኑን መሪ አድርጋለች።
ይሁንና ከእረፍት መልስ ካንያሙኔዛ ኤሪካ በ49ኛው ደቂቃ ከመረብ ያሳረፈችው ግብ ብሩንዲን አቻ አድርጓል።
የሉሲዎቹ የፊት መስመር ተሳላፊ ሴናፍ ዋቁማ ከእረፍት በፊት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብታለች።
በሁለቱ አገራት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ስምምነት የቡድኖቹ የመልስ ጨዋታ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ በደርሶ መልስ ጨዋታ ካሸነፈ በቀጣዩ ዙር ከዩጋንዳና አልጄሪያ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 15ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በሕዳር ወር 2024 ይካሄዳል።