በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለመኸር እርሻ ሥራ አመቺ ዝናብ ይኖራል- የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016(ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በአብዛኞቹ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ለመኸር እርሻ  አመቺ  ዝናብ እንደሚዘንብ  የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በአብዛኞቹ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የሚኖረው ዝናብ ለመኸር እርሻ ሥራ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጿል።

በተለይም ከክረምት አጋማሽ አካባቢ ጀምሮ የዝናብ እጥረት በነበረባቸው የምስራቅ እና የሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች ዝናብ ያገኛሉ።

በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኘው ዝናብ በተለያዩ የውሃ ማቆያ ዘዴ ተጠቅሞ ለእርሻ ሥራ ማዋል እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።

በአንፃሩ የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከመጣው የደመና ሽፋን ጋር ተያይዞ ሊኖር የሚችል እርጥበት ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች በጎ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በምዕራብና በመካከለኛው ምስራቅ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሆኖም ግን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በተዳፋትና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የአፈር መሸርሸር ሊያስከትል ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

ከቀን ወደ ቀን የውሃ መጠናቸው ከፍ እያለ በመጡት እንደ ቆቃ፣ አዋሽ ተፋሰስ፣ ጣና በለሰና ፊንጫ ግድቦች ላይ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ትንበያው አመልክቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም