ቀጥታ፡

የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ በተቀናጀ መንገድ የሚደረጉ ጥረቶች ሊጠናከሩ ይገባል -ባለሥልጣኑ

ቦንጋ፤ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ)፡- በቡና ምርት ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግርን በመቅረፍ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተቀናጀ መንገድ የሚደረጉ ጥረቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን  አሳሰበ። 

"የቡና ጥራት ለጋራ ብልፅግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ ባለስልጣኑ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  ጋር በመተባባር ያዘጋጀው  የቡና ምርት ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር  የሚያግዝ  የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ  ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር፣ "የሀገራችንን የቡና ጥራት ችግር በአግባቡ በመለየት አርሶ አደሩንም ሆነ ሃገርን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ማተኮር አለብን" ብለዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ዋና አላማም የ2016 የቡና ምርት ከመድረሱ በፊት በመወያየት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ አረዳድ ይዘው በብዛትም ሆነ በጥራት ምርቱን በተሻለ መልኩ ለማቅረብ እንደሆነም ተናግረዋል።

"በተለይም እንደ ሀገር የቡና ጥራትን በማስጠበቅ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ይበልጥ ለማጉላት በየደረጃው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ሀገርንም አምራቹንም ተጠቃሚ የምናደርግባቸው ተግባራት በተቀናጀ መንገድ መፈጸም ይገባናል" ሲሉም አክለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ጨምሮ ለቡና ምርት ሰፊ አቅም ያላቸው አካባቢዎች በ2016 የሚመረተውን ቡና ጥራቱን በማስጠበቅ ከደረጃ አንድ እስከ ሶስት በብዛት ማቅረብ እንዲቻል ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ተወካይ አቶ ዮሐንስ መላኩ በበኩላቸው፣ ክልሉ ቡናን ጨምሮ የተፈጥሮ ፀጋን የታደለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ በክልሉ የቡና ሽፋን 560 ሺህ 20 ሄክታር ላይ የደረሰ ሲሆን የቅመማ ቅመም ምርት ሽፋንን ደግሞ ከ88 ሺህ 194 ሄክታር በላይ ማድረስ መቻሉን ገልፀው የሻይ ልማትን ወደ 2 ሺህ 276 ሄክታር ማድረስ መቻሉንም በንግግራቸው አንስተዋል።

ክልሉ በቡና፣ በሻይና ቅመማቅመም ዘርፍ ከክልል ባለፈ ሀገርን መጥቀም የሚችል አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው ባለው አቅም ልክ ውጤት እንዲያስገኝ ሰፊ ርብርብ እየተደረገበት ይገኛል ብለዋል።

በቡናው ዘርፍ የሚታየውን ተግዳሮት በመፍታት ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለአለም ገበያ ለማቅረብ እንዲያስችል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኩል የተዘጋጀው ምክክር ለስኬታማነቱ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም