የኢትዮጵያን እግር ኳስ ስፖርት ውጤት ማጣትን ለመፍታት ሳይንሳዊ የአሰለጣጠን ዘዴን መተግበር ይገባል- በኃይሉ በቀለ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ስፖርት ውጤት ማጣት ችግር ለመፍታት ከታዳጊዎች ጀምሮ ሳይንሳዊ የአሰለጣጠን ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ቴክኒካል አማካሪ በኃይሉ በቀለ ገለፁ።

እግር ኳስ በኢትዮጵያ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑና በበርካቶች ዘንድ በከፍተኛ ጉጉት ከሚዘወተሩ ስፖርቶች ቀዳሚው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራ ተቋም በአህጉሪቱ እንዲመሰረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክታለች።

እግር ኳስ በኢትዮጵያ አንድ ምዕተ-ዓመት የቆየና ሕዝባዊ መሠረት ያለው ስፖርት ቢሆንም በሚፈለገው መልኩ አላደገም።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ቴክኒካል አማካሪ በኃይሉ በቀለ በኢትዮጵያ ያለው የእግር ኳስ አሰለጣጠን ዘይቤ ተመሳሳይ መሆኑን ይናገራሉ።

ለዚህም ደግሞ ለታዳጊዎች፣ ለወጣቶችና ለጀማሪዎች በሚል እንደ ሀገር የተቀመጠ የሥልጠና መመሪያ አለመኖሩ ዋንኛ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።

የአሰለጣጠን ሥርዓቱ ዓለም የደረሰበትን ሳይንሳዊ አሠራር የተከተለ ባለመሆኑ ሳቢያም፤ በእግር ኳስ ስፖርት የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም ሲሉ አክለዋል።

በፊፋ እንደተቀመጠውና በበርካታ የዓለም አገራት እንደሚሰራው የእግር ኳስ ሥልጠና ከስድስት ዓመት ጀምሮ ለህፃናት የሚሰጥ እንደሆነ አቶ በኃይሉ በቀለ አስረድተዋል።

ሆኖም በኢትዮጵያ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ስፖርት ሥልጠና ከ13 እና ከ15 ዓመት የዕድሜ ክልል እንደሚጀምር ገልፀዋል።

ይህም ታዳጊዎች በዕድሜያቸው ማግኘት የሚገባቸውን ሥልጠና እንዳያገኙና በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ለሚመጡት ውጤቶች ደካማ መሆን መነሻ ምክንያት ናቸው ብለዋል።

ይህንንም ለማስተካከል እያንዳንዱ የስፖርት ክለብ የራሱን መመሪያ ማዘጋጀት እንዳለበትና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በየደረጃው የአሰለጣጠን ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት አስረድተዋል።

ሌሎች ሀገራትም የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ስፖርት ሥልጠና መተግበሪያ እንዳላቸውና ኢትዮጵያም ሊኖራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ስፖርት ሥልጠና በኢትዮጵያ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

ትንሹ የሥልጠና ዕድሜ ከ13 ዓመት በታች መሆኑ ግን ከታችኛው የዕድሜ ክልል ጀምሮ እንደማይሰራ ያሳያል።

ስለዚህ የሚመለከታቸው የፌደራል ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊያበጁለት ይገባል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም