ኢትዮጵያ እና መስከረም

(በአየለ ያረጋል)

 መቼስ ሀገሬው መስከረምን ሲናፍቅ ‘ለብቻ’ ነው። በባህሉ፣ በትውፊቱ፣ በስለ-ምኑ፣ በኪነ-ቃሉ እና ስነ-ቃሉ ልዩ ሥፍራ ይሰጠዋል ለመስከረም። እንደ መስከረም ክብር፣ ሞገስ እና ፀጋ የተቸረው የትኛው ወር ይሆን? ማንም! ሀገሬው ለቆንጆ ልጁ ስም ሲያወጣ ‘መስከረም’ እንጂ በሌላ ወር ሰይሞ ያውቃል? አያውቅም። በኢትዮጵያ ምድር መስከረም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት እና አዕዋፋት ራሱ ልዩ ጊዜ ነው።

‘ኢትዮጵያ ነይ በመስከረም…’ እንዲሉ መስከረም ለኢትዮጵያ ውበቷ፣ ቀለሟ፣ ትዕምርቷ፣ የባህር ሃሳቧ መባቻ ነው። ተናፋቂው መስከረም ዝም ብሎ ወር ብቻ አይመስልም።

እውቁ ሠዓሊ እና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ መስከረምን “… በሽቱ መዓዛህ ለውጠው ዓመቱን፤ ይታደስ ያረጀው ፍጥረት ሌላ ይሁን…” ሲል የአዲስ ተስፋና መንፈስ መሻቱን አሳይቷል።

ተወዳጇ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው ደግሞ “… መስከረም ለምለሙ፣ መስከረም ለምለሙ፣ ብሩህ ዕንቁጣጣሽ ደስታ ለዓለሙ…” ትለዋለች መስከረምን ስታዜመው።

እንደየ ንፍቀ ክበቡ ዓመታት በወራት ሲመነዘሩ የራሳቸው መልክና መገለጫ አላቸው። ኢትዮጵያም ከጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር በሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነት ያለው የራሷ የዘመን ቀመር አላት።

ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ባለ 13 ወራት ሀገር ነች። ወራቱም መጸው(መኸር)፣ ሐጋይ(በጋ)፣ ፀደይ(በልግ) እና ክረምት በሚል በአራት ወቅቶች ይከፈላሉ። ወቅቶቹም የራሳቸው ጸባይ፣ ክዋኔ፣ ትውስታና ትዕምርት ይቸራቸዋል። እያንዳንዱ ወርም እንደዚሁ።

ከዘመን መባቻው መስከረም እስከ ማዕዶተ-ዘመኗ ጳጉሜን ወራቱ በሰማይና በምድሩ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውቅራቸው ግላዊ ገጽታ ይነበብባቸዋል። የወራቱ ቅላሜ እና ሕብርነት ልዩ መልክዓ-ኢትዮጵያን ይፈጥራል።

‘የ13 ወር ፀጋ’ የሚለው መጠሪያም በ‘ምድረ ቀድምት’ እስኪተካ ድረስ ለብዙ አሥርት ዓመታት መለያ ሆኖ ዘልቋል። ይህን መለያ ስም ያወጡት እና የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት የሚሰኙት አቶ ኃብተሥላሴ ታፈሠ “ኢትዮጵያ የ13 ወራት ፀሐይ ባለቤት ናት። ስያሜው ከምንም የፖለቲካና ሃይማኖት ጋር ንክኪ የለውም” ብለው ነበር።

የኢትዮጵያ ወራት ስያሜ ከመልክና ግብራቸው ይመነጫል። የወራት መባቻው መስከረም እንደዛው።

ሊቃውንት መስከረምን ሲፈትቱት መስ - 'ዐለፈ፤ ከረመ' ይሉትና “ክረምቱን ማስከረሚያ፤ የጥቢ መባቻ" ወርኅ ሲሉ ያመሰጥሩታል። መስከረም ዘመን ያስረጃል፤ አዲስ ሕይወትና ተስፋ ደግሞ ይደግሳል። አንዳንዴም ይህ ወር ዘመን መለወጫ፣ ዕንቁጣጣሽ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎም ይጠራል፡፡

'አገር፣ ቀለም፣ ዘመን' እንደሸማው በድርና ማግነት ከሚሰባረቅባቸው ወራት አንዱ መስከረም ነው። መስከረም አገርኛ አለባበስ፣ አገርኛ ዝማሬ፣ አገርኛ ጨዋታ፣ አገርኛ ትውፊትና ቀለም በመስከረም በዓላት በተግባር ይታያል። መስከረም ሁለንተናዊ ውበቱ ድንቅ ነው፤ ትዕምርቱም ጉልህ ነው።

የመልክዓ-መስከረም ድምቀት ማሳያዎች

ዘመን መለወጫ

በኢትዮጵያ ዘመን ስሌት ቀለበት መስከረም 1 ቀን ዘመን ይለወጣልና። የዘመን መለወጫ በዓል ‘ርዕሰ ዓውደ- ዓመት’ ይሰኛል። የባህር ሐሳብ ሊቃውንት መስከረም ለምን የዘመን መለወጫ እንደሆነ ሲያትቱ “ብርሃናት /ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው” ይላሉ። በመስከረም ሌሊቱ ከቀኑ እኩል ነው።

ደራሲ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር “ቀዳማይ፣ ርዕሰ ክራሞት፣ መቅድመ አውርኅ፣ ርዕሰ ዐውደ-ዓመት፣ የክረምት ጫፍ መካተቻ፣ የመፀው መባቻ” ይሉታል ወርኃ መስከረምን። እናም ዘመነ ማዕዶቷን፤ ወርኅ ተውሳኳን ‘ጳጉሜን’ ተሻግሮ መስከረምን መሳም ይጓ'ጓ'ል። የመስከረም ጥባት በአያሌው ይሻታል።

'መስከረም ሲጠባ ወደ አገሬ ልግባ …’ እንዲሉ የተሰደዱት በአዲስ ዓመት መባቻ የአገራቸውን አፈር ለመሳም ያማትራሉ። ’አበባዬ ሆይ፤ አበባዬ ሆይ’ የሚሉ ሕፃናት ተስፋና ምኞታቸውን በወረቀት ያቀልማሉ፤ የአበባ ስዕላት ይዘው በየደጃፉ ይሯሯጣሉ፤ የ’ዕደጉ’ ምርቃት ያገኛሉ፤ በደስታ ይንቦጫረቃሉ። በዚህ ድባብ ነው እንግዲህ መስከረምን የግዑዛንም የሕይወታውያንም የነፃነት፣ የተስፋና የፍቅር ወርኅ ተደርጎ የሚናፈቀው።

የብዙ ሺህ ዘመናት ባለታሪኳ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ አዱኛ ሳይርቃት በእርስ በርስ ጦርነት፣ በጠላት ፍላፃዎች እና በድንቁርና ብዛት... ሰንኮፎቿ ሳይነቀሉ በመልከ-ብዙ ምስቅልቅሎሽ ውስጥ ዛሬ ደርሳለች። ጊዜው የኢትዮጵያን መስከረም ያስናፍቃል።

ዕንቁጣጣሽ

መስከረም በአደይ አበባ የሚያሸበርቅ ወር ነው። የነገረ-ዕንቁጣጣሽ የትመጣ መልከ-ብዙ አተያዮች ይጠቀሳሉ። ለምሳሌ “ዕንቁ – ዕፅ አመጣሽ” ብሎ የአበባ መፈንዳት ለማመላከት እንደሆነ የሚጠቅሱ አሉ። ንግሥት ሳባ /አዜብ/ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን የእጅ መንሻ ይዛ ስትሄድ ንጉሡም “ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንሽ” በሚል ቀንና ከሌሊት የሚያበራ ቀለበት ስለሰጣት ነው የሚል አፈታሪክም ይነገራል። የስያሜው መነሻ ያም ሆነ ይህ መስከረም ለመልክዓ-ምድሩ፣ ለሰውና ለእንስሳት ሁሉ ‘ፍስሐ ወተድላ’ የሆነ ወር ነው።

በመስከረም ምድር በዕንቁጣጣሽ ትፈካለች፤ በአበቦች ታጌጣለች፤ ውኆች ይጠራሉ። ሰማዩም የክብረ-ሰማይ ብርሃኑን ያጎላል። ጥቁር ደመና ጋቢ ይገፈፋል፤ ክዋክብት እንደፈንዲሻ በዲበ-ሰማይ ይደምቃሉ። ዕጽዋትና አዝዕርት እንቡጦች ይፈነዳሉ። የመብረቅ ነጎድጓድ ተወግዶ የሰላምና የሲሳይ ዝናብ ይዘንባል።

እንስሳት የጠራ ውሃ እየጠጡ፣ ለምለም ሳር እየነቸረፉ ይቦርቃሉ። እርሻ የከረሙ በሬዎች፣ ጭነት የከረሙ አህዮች መስከረም አንጻራዊ የእፎይታ ወራቸው ነው። ነጎድጓድ በአዕዋፋት ዝማሬ ይተካል። ንቦች አበባ ይቀስማሉ፤ ቀፏቸውን ያደራሉ። ቢራቢሮ ሳትቀር ‘በመስከረም ብራ ከኔ በላይ ላሳር..’ ብላ ትከንፋለች።

በ’ዕንቁጣጣሽ’ ምድር ብቻ አይደለችም የምትዋበው። መስከረም ለሰው ልጆችም በተለይም ለወጣቶች የፍቅር፣ የእሸት እና የአበባ ወር ነው። የሰላም፣ የንጹህ አየር፣ የጤና ድባብ ያረብባል። የጋመ በቆሎ እሸት ጥብስ፤ ቅቤ ልውስ፤ ቅቤ በረካ ይናፈቃል። የተጠፋፋ ዘመድ አዝማድ ይገናኛል። ‘ሰኔ መጣና ነጣጠለን’ ብለው ወርኃ ሰኔን የረገሙ ተማሪዎች ተናፋቂያቸውን ያገኛሉና ‘መስከረም ለምለም’ ብለው ያሞካሹታል። የገበሬው የሰብል ቡቃያ ያብባል፤ እሸት ያሽታል። ጉዝጓዝ ሣር፣ ትኩስ ቡና ይሽታል።

ደመራ ወመስቀል

ሊቃውንት የደመራን የትመጣን ሲፈትቱ ‘ደመረ፣ ተሰባሰበ’ ይሉታል። ጎረቤት፣ የሩቅ የቅርብ ዘመድ አዝማድ ተደምሮ የሚከውነው ነውና።

ነገረ መስቀሉ እምነቱ፣ ባህሉ፣ ትውፊቱ ብዙ ነው። መስቀል በሃይማኖተ-አበው ሀተታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን፣ ለፍጡር የሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጸበት ዓርማ ነው። በዚህም መስቀልን አማኝ ምዕመናን እና ካህናት የደኅንነትና የእምነት ምልክታቸው፤ የርኩስ መንፈስ ማባረሪያ መሳሪያቸው አድርገው ይመለከቱታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መስከረም 10 ቀን ‘ተቀጸል ጽጌ’ በሚል የክርስቶት መስቀል ግማድ (ቀኝ እጁ ያረፈበት ክፋይ) ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ኢትዮጵያ የገባበትን ቀን ታከብረዋለች፤ መስከረም 17 ቀን ደግሞ መስቀሉ የተገኘበትን። መስከረም 16 እና 17 ቀን የሚከበረው የደመራ መስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮው ባለፈ ባህላዊ ትውፊትነቱ የጎላ በመሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ይናፈቃል።

ደመራና መስቀል የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ አብሮነት፣ የምስጋና፣ የተስፋ… እሴቶች የሚገለጹበት ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ክብረ-በዓል ነው። ደመራ እና መስቀል በዓላት ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓል ቢሆንም እንደየ አካባቢው ባህል፣ መንፈሳዊነት፣ ትውፊት፣ ዕውቀት አገርኛ ህብር ጥበባት የሚጎሉበት፣ አገር የውበት አክሊል የምትደፋበት ዕለት ነው።

መስቀል የዓለማችን የማይዳሰስ የኢትዮጵያ ወካይ ቅርስ መዝገብ ሥር ሰፍሯል። በመስቀል አገርኛ ቀለም ይጎላል። 'አገር፣ ቀለም፣ ዘመን' እንደሸማው በድርና ማግነት ይሰባረቃሉ። የባህር ማዶ ጎብኚዎች በአግራሞትና መደነቅ ሲናገሩ ይደመጣሉ። የዕንቁጣጣሽ ተከታይ የመስከረም መልክ ነው መስቀል።

የደመራ አደማመር እና ማብራት ሥነ-ሥርዓት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተመሳሳይ እንዳልሆነ ደራሲ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር ይተርካሉ። በትግራይ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በዋግኸምራ፣ በአዊና በከፊል ጎጃም ደመራ ማታ ላይ ተደምሮ ንጋት ላይ ይለኮሳል። በከፊል ጎጃም፣ በሸዋ፣ በአዲስ አበባ፣ በጉራጌ፣ በጋሞ፣ በወላይታና ሌሎች የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ እንደየ አካባቢው ተለምዶ መስከረም 16 ከእኩለ ቀን ጀምሮ እስከ አመሻሽ ድረስ ደመራው ይለኮሳል።

መስቀል በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ርዕሰ ዓውደ-ዓመት ይመስላል። በደቡብ ኢትዮጵያ መስቀል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባህላዊ ጎኑ ይጎላል። ጉራጌዎች፣ ጋሞዎችና ሌሎችም መስቀልን ከሁሉም በዓላት የበለጠ ይናፍቁታል። የተራራቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት የፍቅር፣ የደስታና የእርቅ በዓል ነው መስቀል። በጋሞ ብሔረሰብ ባህል በዋዜማው ሰው ቢሞት እንኳን በሌሊት ተወስዶ ይቀበራል እንጂ ለቅሶ እንደማይለቀስ ይነገራል፤ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳቱም ልዩ መኖ እንደሚቀርብላቸው ይነገራል። ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚባለው በጋሞዎች ደግሞ ‘ለመስቀል ያልሆነ ዱንጉዛ ይበጣጠስ’ በሚመስል መልኩ የባህል ልብስ አለባበስ እንደሚዘወተር መምህር ካሕሳይ (በሕብረ-ብዕር ድርሰታቸው) ጽፈዋል።

መስቀል በጉራጌዎች ዘንድ እንደ አውራው በዓል ይቆጠራል። ለመስቀል ዓመቱን ሙሉ ዝግጅት ይደረጋል። አባወራው ሰንጋ ለመግዛት፣ እማወራ ማጣፈጫውን ለማዘጋጀት፣ ወጣቶች ደመራና ደቦት ለማዘጋጀት፣ ልጆች ምርቃት ለመቀበል የየራሳቸውን ይዘጋጃሉ። ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ የሚጠያየቅበት፣ ለትዳር የደረሱ ሚስት የሚያጩበትና የሚመርጡበት ጥላቻና ቂም በፍቅርና በይቅርታ የሚታደስበት ነው። በጉራጌዎች ዘንድ መስቀል ትልቅ ቦታ ይቸረዋል።

መስቀል እንደየአካባቢውና ባህሉ የሚናፈቅበት ዕልፍ ገጽታዎች አሉት። ለምሳሌ እኔ በተወለድኩበት ገጠራማ አካባቢ ያለውን በወፍ በረር እንቃኘው!

በደመራ ዋዜማ ቀናት ልጆች ተራራ ለተራራ፣ ወንዝ ለወንዝ፣ ቋጥኝ ለቋጥኝ በልጅነት ወኔና ስስት በመዞር ለደመራ የሚሆን እንጨት፣ አደይ አበባ፣ ደቦት(ችቦ) ያጠራቅማሉ። ልክ መስከረም 16 አመሻሽ ከብቶች ወደ ግርግም ከገቡ የመንደሩ ወጣቶች ወደ ‘አፋፍ’ ይወጣሉ። ደመራ ወደሚደመርባት ሥፍራ። ሁሉም የአንድ ዕድር አባላት ቤተሰብ ተወካዮች ባሉበት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት የደመራው ሥራ ይጠናቀቃል። ደመራው ሲጠናቀቅ ወደየ ቤታችን እንበታተናለን። (አዲስ አበባን ጨምሮ በከተሞች እንደሚደረገው በመስከረም 16 አመሻሽ ደመራው አይለኮስም። ይልቁኑ መስከረም 16 ለ17 አጥቢያ ጀምሮ ይለኮሳል እንጂ።)

ለመስከረም 17 አጥቢያ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ሁሉም ሰው ከየቤቱ ደቦቱ (ችቦውን) እየለኮሰ ‘እዮሃ ደመራ’ እያለ ወደ ደመራው ሥፍራ ይተማል። እንደየ ግለሰቡ ቤት እስከ ሦስት ኪሎ ሜትር ድረስ መጓዝ ሊጠይቅ ይችላል። የመስከረም እኩሌታ አረንጓዴያማ ውብ ማሳ ከየቤቱ ከሚወጡ የችቦ እሳት ነበልባል ብርሃን ይታጀባል። ከሌሎች አጎራባች የመንደር ደመራዎች ቀድሞ ለመለኮስ ጉጉቱ የትየለሌ ነው።

ከቤት እስከ ደመራው ሥፍራ እስኪደርሱ ድረስ ሰዎችን፣ በረት ያሉ ከብቶቹንና የጓሮ አዝመራውን ጨምሮ ሕይወታዊያንን በሙሉ “እንጎረጎባህ፤ እንጎረጎባችሁ” ይባላል። የተጠያቂው ሰው ምላሽ ደግሞ “ዓመት ዓመቱን ያድርስህ” የሚል ይሆናል። ከደመራ ግጥም ተዘውታሪ ስንኞች መካከልም፡-

“እዮሃ አበባዬ፣ መስከረም ጠባዬ፣

እዮሃ አረሬ አረሬ፣ መስቀል ጠባ ዛሬ፣

በሸዋ በትግሬ…” የሚለው ይጠቀሳል።

ከደመራው ሥፍራ ስንደርስ የ’እንጎረጎባህ!’ ድምፆች ይበረታሉ። የ’ዓመቱን ያድርስህ’ መልስ ካልሆነም እኩይ አፀፋ ይኖራል። ሁሉም ከተሰባሰበ በኋላ ደመራን የሚያሞካሹና የአዲሱን ዓመት መልካምነት የሚመኙ ‘እዮሃ አበባዬ” ግጥሞች እየተደረደሩ ደመራው ሦስት ጊዜ እንቧለሌ ይዞራል። በዕድሜ ታላቅ እና የተከበረ ሰው በቅድሚያ ደመራውን ይለኩሳል። ቀጥሎ ሁሉም ወደ ደቦቱን(ችቦውን) ወደ ደመራው ውስጥ ያስገባል። ደመራውም ይቀጣጠላል። የእሳቱ ነበልባል በመስከረም የንጋት ውርጭና ብርድ ላይ ያይላል።

ሁሉም በደመራው ዙሪያ ተኮልኩሎ የክረምት ወራት ትዝታ ይነሳል፤ ሹፈት፣ ቀልድና ቁምነገር በየፈርጁ ይሰለቃል። ሌሊቱ የአህያ ሆድ እስኪመስል ይቀጥላል። የተጣላም ይታረቃል። የደመራው አምድ (ምሰሶ) አወዳደቅ ለማየት ሁሉም በጉጉት ይጠብቃል። ምሰሶው ወደ ምሥራቅ ከወደቀ የጥጋብ ዓመት፤ ወደ ምዕራብ ከሆነ ግን የችጋር ዓመት ተደርጎ ይታመናል።

ከደመራው ሁነቶች አንዱ ባህሉ የበቆሎ እሸት ናፍቆት ነው። የደመራው ምሰሶ ከወደቀ በኋላ በአቅራቢያ ካለ የበቆሎ ማሳ በቆሎ እሸት ይመጣል። በመስቀል ደመራ ፍም ተጠብሶ ይበላል። ባለበቆሎው ሰው ዓመታዊ ደንብ ስለሆነ የበቆሎ ማሳዬ ተጎዳብኝ ብሎ አይቆጣም። ከደመራው ዓመድ ግንባራችን ላይ መስቀለኛ ምልክት ማድረግ እና ‘የዛሬ ዓመት አድርሰኝ’ ስለት ይቀጥላል።

ሰማዩ የአህያ ሆድ ሲመስል ልጆች በደቦ ወደ መንደር ለመንደር በመዞር ‘እንጎረጎባችሁ’ እንላለን። የቤቱ ባለቤትም በሳህን፣ ጣሳ ወይም ሌላ ዕቃ ጤፍ ዱቄት ይሰጣል። የሰበሰብነውን ዱቄት ይዘን ወደ ደመራው ሥፍራ እንመለሳለን። በደመራው ጉባዔ ተወስኖ ከዕድሩ ለተመረጠች ቀጭን እመቤት (ባለሙያ ሴት) ዱቄት ይሰጣትና በ17 ምሽት ለሚኖረው የእራት ሰዓት ዝግጅት በአነባበሮ መልክ ዱቄት አብኩታና ጋግራ ታቀርባለች።

መስቀል የወል ክብረ በዓል ነው። የመስቀል ዕለት (መስከረም 17) በግ ይታረዳል። እህል ውሃ ቀርቦ የመንደሩ ሰው በጋራ ሲጫወት ይውላል፤ በሕብረት ይበላል። ለመስቀል የተጣላ ጎረቤት ይታረቃል። ልጆች በሕብረት ይቦርቃሉ። የመስቀል ትዝታ በእኛ መንደር ይናፈቃል። ሁሉም እንደየ ቀየው ትውፊት እና ልማድ ይህን ሁነት ይናፍቃል….!!

ጊፋታ

ጊፋታ/ ግፋታ ማለት ትርጉሙ በኩር ወይም ታላቅ ማለት ሲሆን በለኬላ ትርጓሜው መሻገር ማለት ነው፡፡ በወላይታ ብሔረሰብ አዲስ ዓመት አንድ ብሎ የሚጀመርበት የአዲስ ዓመት መግቢያና የብርሃን ጊዜ ማብሰሪያ ነው፡፡ ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውንም ይገልጻል፡፡ ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው፡፡

በወላይታ ብሔረሰብ ዘንድ መስከረም ወር በገባ ከቀን 14 እስከ 20 መካከል የሚውለው እሑድ አዲሱን ዓመት የሚቀበሉበር ዕለት ይሆናል፡፡ በዓሉ የሚውልበት እሑድ ስሙም ‹‹ሹሃ ወጋ›› የእርድ እሑድ ይባላል፡፡

እሑድ የአዲስ ቀን ብሥራትም ነው፡፡ ቀጣዮቹ የሳምንቱ ቀናት የየራሳቸው ስያሜና አከባበር አላቸው። ለአብነት ‹‹ጋዜ ኦሩዋ›› ማንሳት ይቻላል። የአዲስ ዓመት አራተኛ ቀን ነው። የሰፈሩ ወጣቶች በየመንደሩ በታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች ደጅ ተሰባስበው የግፋታ በዓል ባህላዊ ጨዋታ የሆነውን ጋዜ በጋራ ሆነው ‹‹ሀያያ ሌኬ›› እያሉ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው የሚጫወቱበትና ልጃገረዶችን ሎሚ በመለመን የሚፈልጓትን የሚመርጡበት ጨዋታ የሚጫወቱበት ቀን ነው፡፡

በዕለቱ ልጃገረዶች አንድ ላይ ሆነው በየቡድን ቁጭ ብለው ወንዴና ሴቴን ከበሮ እየመቱ ‹‹ወላወላሎሜ›› እያሉ የሚመርጡትን ወንድ ሎሚ በመስጠት የሚመርጡበት፣ እንዲሁም ሴቶች ለሚዜነትና ለጓደኝነት ከመረጧት ሴት ጋር በጥርስ አንድ ሎሚን ለሁለት የሚከፋፈሉበትና ስማቸው ሲጠራሩ ‹‹ሎሜ ሎሜ›› የሚባባሉበት ጨዋታ የሚጫወቱበት ዕለት ጋዜ ኦሩዋ ነው፡፡

ግፋታ ሲሸኝ ጥቅምት በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ማክሰኞ ሆኖ የሽኝት በሬ ታርዶ ከተበላ በኋላ ቶክ ጤላ የተባለውን ምሽት በችቦ ያባርራሉ፡፡ ዜማ በተቀላቀለበት ጩኸት ችቦ ይዘው ‹‹ኦሎ ጎሮ ባ! ሳሮ ባዳ ሳሮ ያ!›› ይላሉ፡፡ ትርጓሜውም ጊፋታ በሰላም ሄደሽ በሰላም ነይ! ማለት ነው፡፡

ዮ …ማስቃላ

በጋሞዎች ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው «ዮ ማስቃላ» የዘመን መለወጫ በዓል በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ቅበላው ተከብሮ በዚሁ ወር መጨረሻ «ዮ ማስቃላ» ሽኝት በዓል በድጋሚ በድምቀት ይከበራል። መስከረም ወር የመጀመሪያው ቀን በጋሞ ዞን ”ሂንግጫ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህም አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጅት የሚደረግበት ቀን ነው።

ጋሞዎች ዓመቱን ሙሉ ገንዘብ በመቆጠብ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ይደረጋል። ወንዶች ለበዓሉ የሚሆን ሠንጋ መግዣ፣ ለልጆች ልብስ እና ጌጣጌጥ ማሟያ፤ እናቶች ደግሞ ለቅቤ፣ ለቅመማቅመም፣ ለባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች እህል መግዣ የሚሆን ገንዘብ ያጠራቅማሉ።

በጋሞ ዞን የማስቃላ በዓል ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንሳስት እና ለአዕዋፋትም ጭምር ነው ተብሎ ይታመናል፤ በዕለቱ ምግብ ከሰው አልፎ ለእንሳስት እና ለአዕዋፍም ይትረፈረፋል። ለከብቶችም የግጦሸ መሬት በየአካባቢው ይከለላል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የተጣሉ ታርቀው፣ የተራራቁ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች ተሰባስበው በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩ ማድረግ የጋሞ ማስቃላ በዓል መገለጫ ነው።

በጋሞ ብሔረሰብ የሚከበረው የማስቃላ በዓል በሶፌ ሥርዓት የታጀበ ነው። የቀደመው ዓመት ማስቃላ በዓል ከተከበረ በኃላ የተጋቡ ሙሽሮች ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ማምሻውን በአደባባይ ከመላው ሕብረተሰብ ጋር የሚቀላቀሉበት እና ሁለቱም ተጋቢ ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ደስታቸውን የሚገልፁበት ሥርዓት ነው።

የመጨረሻው የማስቃላ ሽኝት በዓል ነው፤ ይህ ሥርዓት እንደየአባወራው አቅም በፈቀደ መጠን የሚፈፀም ነው። በዚህ ዕለት ሁሉም ያለ ፆታ ልዩነት በአደባባይ ላይ ወጥተው ያኑረን እስከ ወዲያኛው እንኖራለን እያሉ ይጨፍራሉ። ከዚህ በኋላ ለመጪው ዓመት በሰላም በጤና ያድርሰን ተባብለው ፈጣሪን በመማፀን ዝግጅቱ ይቋጫል።

ያሆዴ መስቀላ

የክረምቱ ወራት አልፈው መስኩ በልምላሜና በአደይ አበባ ሲያሸበርቅ በሃድያዎች ዘንድ ትልቅ ዝግጅት አለ - ያሆዴ መስቀላ።

“ያሆዴ“ ማለት እንደ ብሔሩ የባህል ሽማግሌዎች ትርጓሜ እንኳን ደስ አላችሁ፤ የሚል የብስራት ትርጉም ያለው ሲሆን ”መስቀላ” ማለት ደግሞ ብርሃን ፈነጠቀ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ያሆዴ መስቃላ ብርሃን ፈነጠቀ እንኳን ደስ አላችሁ የሚል ትርጉም አለው። በዓሉ በወርኃ መስከረም 16 የሚከበር ሲሆን ወሩ ብርሃን፣ ብሩህ ተስፋ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ረድኤት፣ በረከት የሚሞላበት ተምሳሌት ወር ተደርጎ ይቆጠራል።

የሃድያ አባቶች ”ከባለቤቱ የከረመች ነፍስ በያሆዴ መስቀላ ትነግሳለች“ የሚል ብሂል አላቸው። የሃድያ አባቶች እንደ ዘመን መለወጫ የመጀመሪያ ቀን አድርገው በመውሰድ ማንኛውንም ዓይነት ክስተት ከዚያ ጋር አያይዘው እንደሚቆጥሩ ይነገራል።

በዓሉ ከመድረሱ በፊት ሁሉም የቤተሰብ አባላት በዓሉን ለማድመቅ የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። በብሔሩ አባቶች አብሮነታቸውን ከሚያጠናክሩባቸው ማኅበራዊ እሴቶች መካከል አንዱ ቱታ/ሼማታ/ሲሆን ይህ ማለት በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተደራጀ ቋሚ የሆነ ከአራት እስከ ስምንት አባላትን የያዘና በሥጋ ቅርጫ የተደራጀ ማኅበር ነው።

የዚህ ማኅበር አባላት ግንኙነት ያላቸው የሚተሳሰቡ የኢኮኖሚ አቅማቸውም ተቀራራቢነት ያለው ሲሆን በመቀናጀት የበዓሉ እለት ከመድረሱ በፊት በጋራ ገንዘብ ማስቀመጥ ይጀምራሉ፤ በበዓሉ ወቅትም ለእርድ የሚሆን በሬ መግዣ ገንዘብ እንዳይቸገሩና በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ሕብረታቸው ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለከብቶች የግጦሽ ሳር የሚሆን ቦታ ከልሎ በማስቀመጥ የበዓሉ ቀን ከብቶች ተለቀውበት እንዲጠግቡ የሚደረግ ሲሆን በአዲስ ዓመት መግቢያ እንኳን የሰው ልጅ እንሰሳትም ቢሆኑ መጥገብ እንዳለባቸው እንዲሁም የጥጋብ ዘመን እንዲሆን በብሔሩ በዓሉ ለሰው ብቻ ሳይሆን እንሰሳትም ሆዳቸው ሳይጎድል አዲሱን ዓመት መቀበል እንዳለባቸው በመታመኑ ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል።

 ኢሬቻ

ኢሬቻ ከመስከረም ደማቅ መልኮች አንዱ ነው። ኢሬቻ የዘመነ መፀው መጀመሪያ ሁነት ነው። የኢሬቻ ክብረ በዓል ኢሬቻ ቢራ (መልካ) በሐይቆች ወይም በወንዞች ዳር የሚከበር ነው።

ከክረምት ወደ መፀው መሸጋገርን ምክንያት በማድረግ የሚከወን የምስጋና በዓል ነው። በኦሮሞ ዘንድ ለዘመናት የሚከበር እና ከገዳ ሥርዓት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይነገራል።

ኢሬቻ ከመስቀል በኋላ ይከበራል። በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የ'ሆራ አርሰዲ' እንዲሁም ‘ሆራ ፊንፊኔ’ ከፍተኛ ሕዝብ ቁጥር በታደመበት በድምቀት ይከበራል። በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለያዩ ክዋኔዎች እንዲሁ ይከበራል።

ኢሬቻ ለፈጣሪ (ዋቃ) የክረምት ወቅትን በማሳለፉ፣ ወይንም ወደ አዲስ ዓመት በማሸጋገሩ የሚቀርብ ምስጋና ነው። ‹‹ዋቃ›› ፍጥረተ ዓለምን ያስገኘውና ሒደቱንም የሚያስተናብረው አንድ አምላክ ማለት ነው፡፡

‹‹ኢሬቻ ሰላም ነው፣ ሰላም ጥልቅ ትርጉም አለው፣ ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከፈጣሪው ጋር ሰላም ሊኖረው ይገባል፤›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የክብረ በዓሉ ጭብጥ ነው፡፡

ለሕዝቡና ለአገሩ ምርቃትና መልካም ምኞት የሚገለጽበትም ነው-ኢሬቻ። ታዲያ ማንኛውም ሰው ወደ በዓሉ ሥፍራ ሲሄድ አለባበሱን ማሳመር ይጠበቅበታልኢሬቻ ከመስቀል በኋላ ይከበራል።

ቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የ'ሆራ አርሰዲ' እንዲሁም ‘ሆራ ፊንፊኔ’ ከፍተኛ ሕዝብ ቁጥር በታደመበት በድምቀት ይከበራል። በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለያዩ ክዋኔዎች እንዲሁ ይከበራል።

ኢሬቻ እንደ ዕንቁጣጣሽ በመስከረም ጥባት ውሃ ጎድሎ፣ የተራራቀ ዘመድ አዝማድ የሚገናኝበት ነው።

በተለያዩ ጸሐፍት እንደተጠቀሰው፣ ኢሬቻ አንድም ‘ዋቃ’ ከብርድና መብረቅ፣ ከጎርፍ፣ ከአውሎ ነፋስ እና መሰል የክረምት ተፈጥሯዊ ክስተቶች ጠብቆ ወደ ብራ እና ፀሐያማው የመፀው ወቅት በሰላም ስላሸጋገረ፣ አንድም በዋቃ ፈቃድ ዝናብ ዘንቦ፣ መሬቱ ረስርሶ፣ አዝመራው ለምልሞ፣ መልካም ፍሬ በመታየቱ፣ እሸት በመስጠቱ ስለማያልቀው ቸርነቱ ለማመስገን ነው። ከክረምቱ ጨለማ ወደ ብርሃን የማለፍ ብሥራት ነው ኢሬቻ።

በሌላ በኩል ደግሞ መጪው አዲሱ ዓመት የተባረከና የተቀደሰ፣ የደስታና የብልፅግና፣ የተድላና ፍስሃ ይሆን ዘንድ መልካም ምኞትን የመግለጫ በዓልም ነው።

በኢሬቻ ክዋኔ አባ ገዳዎችና የሕዝብ መሪዎች ይመርቃሉ። በኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ አለባበሱን በማጌጥ ወደ ክብረ-በዓሉ የሚያመሩ ኢሬቻ አክባሪዎች እርጥብ ሳር እና አደይ አበባን ይይዛሉ።

ከኢሬቻ ክብረ-በዓል የምርቃት ስንኞች መዘን እንሰናበት።

“… ለምድራችን ሰላም ስጥ!

ለወንዞቻችን ሰላም ስጥ!

ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!

ለሰውም ለእንስሳቱም ሰላም ስጥ!

ከእርግማን ሁሉ አርቀን!

ከረሃብ ሰውረን!

ከበሽታ ሰውረን!

ከጦርነት ሰውረን!

ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! (አሜን! አሜን! አሜን!)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም