ኢትዮጵያ በ78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እያከናወነች ነው - አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በ78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እያከናወነች ነው - አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 11/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እየሰራች መሆኑን በተ.መ.ድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ገለጹ።
78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ "ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥና ዘላቂነት" በሚል መሪ ኃሳብ በመከናወን ላይ ይገኛል።
በተ.መ.ድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ኢትዮጵያ በጉባዔው ያላትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ከዋናው ጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረግ መቻሏን ጠቁመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መምከራቸውን ጠቁመዋል።
ከዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋር አካላት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና በባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ውይይት ማድረጋቸውንም እንዲሁ።
በዚህም አገራቱ ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞና የሰላም ሂደት በትክክለኛ አቅጣጫ እየሄደ መሆኑን የጋራ መግባባት ተፈጥሮበታል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራትና ተቋማት በተዘጋጁ የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች ተሳትፎ በማድረግ ያላትን አቋም ማስረዳቷንም ገልፀዋል።
በዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሻሻያ እንደሚያስፈልግና አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድምጿን ማሰማቷን ተናግረዋል።
በተለይም ደግሞ በጠቅላላ ጉባዔው ኢትዮጵያ ያላትን እውነታ በሚገባ ማስረዳትና አቋሟንም በትክክል ማንፀባረቅ መቻሉን አመልክተዋል።
ከዓለም አቀፍ ተቋማትና የተለያዩ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች ፍሬያማ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ ያሳዩት ፍላጎት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአገር አቀፍ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ያላትን ምልከታና አቋም የምታንፀባርቅበት የፖሊሲ ንግግር በጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንደምታደርግ ጠቁመዋል።
በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ያለው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እስከ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።